ቀጥታ፡

ሀገራዊ ለውጡ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ታሪክ ቀያሪ ስኬቶች እንድታስመዘግብ አድርጓል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2018(ኢዜአ) ፦ ሀገራዊ ለውጡ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የምርታማነት አቅም በማጎልበት የምግብ ሉዓላዊነትን እንድታረጋግጥ የሚያስችሉ ታሪክ ቀያሪ ስኬቶች የተመዘገቡበት መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር "የግብርና ምርታማነት ለምግብ ሉዓላዊነትና ለሀገራዊ ክብር" በሚል መሪ ሐሳብ በለውጡ ዓመታት በግብርናው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።


 

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ እውን ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ፣ ግብርናው የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ከሚደግፉ አምስት ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል አንዱ ሆኖ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል።

በለውጡ ማግስት ዘርፉን ከባህላዊ ወደ ዘመናዊ አሰራር ለማሸጋገር በተከናወኑ የተቀናጁ ተግባራት፣ በስንዴ ምርት ራስን ከመቻል ባለፈ ለውጭ ገበያ የሚሆን ምርት ማምረት ተችሏል።

በመድረኩም የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) ፣ የግብርና ዘርፍ ሙያተኞችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ የግብርና ዘርፍ በምግብ ደኅንነት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በወጪ ንግድና በአየር ንብረት ላይ ግንባር ቀደም የኢኮኖሚ ድርሻ አለው ብለዋል።


 

ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ የግብርና ሥርዓት በኋላቀር አሰራርና በአየር ንብረት ለውጥ ይፈተን እንደነበር አስታውሰው አዝጋሚ የምርታማነት የአስተራርስ ሥርዓቱም የግብርናው ዘርፍ ታሪክ የሚያጎደፍና ምርታማነትን የሚያቀጭጭ ሂደቶች ውስጥ ማለፉን አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ ማግስትም የግብርና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ የፖሊሲና ስትራቴጂ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አንስተዋል።

በዚህም ሀገራዊ ለውጡ የግብርናው ዘርፍ የኢትዮጵያውያን የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ የሚያስችል ታሪክ ቀያሪ የምርታማነት ምዕራፍ ውስጥ ገብቷል ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ተግባራዊ የተደረገው የግብርና ምርታማነት የመኸርና የበጋ መስኖ ስንዴ እመርታዊ ውጤት መገኘቱን አስታውቀዋል።

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የፖሊሲ አቅጣጫም ለዘመናት ስንዴ ሲሰፈርለት የነበረን ሀገርና ህዝብ የምግብ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ እራስን ወደ መቻል እመርታዊ ሽግግር እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

በሌማት ትሩፋትና በአረንጓዴ አሻራም የምግብና የሥነ- ምግብ ሥርዓትን የሚያሻሽል ውጤታማ የምርታማነት አቅም መፈጠሩን አንስተው በቀጣይም የኢትዮጵያን የተሟላ የግብርና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የተመዘገቡ ስኬቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሠይፈ ደርቤ፥ የፓናል ውይይቱ የሀገራዊ ለውጡን 8ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የግብርናውን ጉዞና ስኬቶች ለመዳሰስ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም፣ ሀገራዊ ክብርና ሉዓላዊነት እንዲሁም ገፅታን መገንባትና ማስጠበቅ የኢዜአ ዋነኛ ተልዕኮ መሆኑን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ የመጋቢት 24 ዋዜማ የሚካሄደው የግብርና ምርታማነት ለምግብ ሉዓላዊነትና ሀገራዊ ክብር ወሳኝ በመሆኑም ፓናሉ መዘጋጀቱንና ቀጣይነት እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

የግብርና ምርታማነትን በመጎናጸፍ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ትርክትን የመቀየርና የተረጂነት እሳቤን የመስበር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር መድረኩን እንዳዘጋጀው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም