ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከትግራይ ክልል ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ የመጀመሪያው ዙር መድረክ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 23/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከትግራይ ክልል ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ የመጀመሪያው ዙር መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት ከመጋቢት 23 እስከ 25 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ መግለጹ ይታወቃል።


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከትግራይ ክልል ባለድርሻ አካላት ጋር የመጀመሪያውን ዙር የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ማካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩ የሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች፣በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ በትግራይ ክልልና በአዲስ አበባ ከ22 ጊዜ በላይ የውይይት መድረኮች ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የሀገራዊ ምክክሩን የአጀንዳ ማሰባሰብና ልየታ ስራ በትግራይ ክልል ማድረግ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ ባለመኖሩ የመጀመሪያውን ዙር የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምረናል ብለዋል።


 

በዚህ ዙር ያልተሳተፉ የትግራይ ክልል ተሳታፊዎችን በቀጣይ ለማወያየት ኮሚሽኑ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

መድረኩ አጀንዳ ከማሰባሰብ ባለፈ ለዋናው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮች የሚለዩበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አካታችና ገለልተኛ ሆኖ እንደሚሰራ ገልጸው፥ የትግራይ ክልል በምክክሩ ሂደት ተሳታፊ እንዲሆን እድል መመቻቸቱን ገልጸዋል።

ከጥላቻ ፍቅርን ከውዝግብ ምክክርን በማስቀደም ለሁላችንም የምትሆን ሀገር መገንባት የሚያስችል ውይይት የሚደረግበት መድረክ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አምባሳደር መሀመድ ድሪር በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ እስካሁን የአጀንዳ ማሰባሰብንና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ሲያካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ እስካሁን ያካሄዳቸው ውይይቶች አሳታፊ እና አካታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ አለመግባባቶችን በምክክር መፍታት ባህል እንዲሆን የማድረግ ዓላማን ይዞ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም