ቀጥታ፡

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከ52 ዓመታት በኋላ ለዓለም ዋንጫ አለፈች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የክፍለ አህጉራት የመጨረሻ ማጣሪያ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጃማይካን 1 ለ 0 አሸንፋለች።


 

ከእኩለ ሌሊት በኋላ በሜክሲኮ አክሮን ስታዲየም የተካሄደው ጨዋታ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለ ግብ አቻ በመጠናቀቁ ወደ ጭማሪ ሰዓት አምርቷል።

በጭማሪ ሰዓት የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ አክሴል ቱዋንዜቤ በ100ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል። የጨዋታው ኮከብም ሆኗ ተመርጧል።

በጨዋታው የማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ሀገር የተሻለ ብልጫ በመውሰድ ተጫውታለች።


 

ውጤቱን ተከትሎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከ52 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫ በማለፍ ታሪክ ሰርታለች።

የማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ሀገር ለመጨረሻ ጊዜ በውድድሩ ላይ የተሳተፈችው እ.አ.አ በ1974 በጀርመን (በወቅቱ አጠራሯ ምዕራብ ጀርመን) አስተናጋጅነት በተካሄደው 10ኛው የዓለም ዋንጫ ነው።

አሁን ለሁለተኛ ጊዜ በውድድሩ ላይ ትከፈላለች።

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የምትሳተፍ 10ኛ የአፍሪካ ሀገርም ሆናለች።

ሞሮኮ፣ ሴኔጋል፣ ግብጽ፣ ኮትዲቯር፣ አልጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና እና ኬፕ ቨርዴ ለዓለም ዋንጫ ያለፉ የአፍሪካ ሀገራት ናቸው።

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በዓለም ዋንጫው በምድብ 11 ከፖርቹጋል፣ ኡዝቤኪስታን እና ኮሎምቢያ ጋር ጨዋታዎቿን ታደርጋለች።

አፍሪካ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ 10 ሀገራት በዓለም ዋንጫው ታሳትፋለች።

ጃማይካ ከ28 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫው የመመለስ ውጥኗ አልተሳካም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም