ቀጥታ፡

ጣልያን ከዓለም ዋንጫ ውጭ ሆነች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የአውሮፓ ዞን የፍጻሜ ማጣሪያ ጨዋታዎች ማምሻውን ተደርገዋል።

ትናንት ማምሻውን በቢሊኖ ፖልጄ ስታዲየም በተካሄደውጨዋታ ቦስኒያ እና ሄርዞጎቪና ጣልያንን 4 ለ 1 በመለያ ምት አሸንፋለች።

ሁለቱ ቡድኖች በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

ሃሪስ ታባኮቪች ለቦሲኒያ፣ ሞይስ ኪን ለጣልያን ግቦቹን አስቆጥረዋል።

የጣልያኑ አሌሳንድሮ ባስቶኒ በ41ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

በጭማሪ 30 ደቂቃ ተጨማሪ ጎል ባለመቆጠሩ አሸናፊውን በመለያ ምት መለየት ግድ ሆኗል።

በዚህ ቦሲኒያ 4 ለ 1 በማሸነፍ ከ12 ዓመታት በኋላ ለዓለም ዋንጫው ማለፏን አረጋግጣለች።

ሶስት ሚሊዮን ህዝብ ያላት ቦሲኒያ ለሁለተኛ ጊዜ በዓለም ዋንጫው ትሳተፋለች።

ጣልያን ከ20ኛው የዓለም ዋንጫ በኋላ ዓለም ትልቁ የእግር ኳስ መድረክ የመመለስ ህልሟ አልተሳካም። 

አዙሪዎቹ ለሶስት ተከታታይ የዓለም ዋንጫ ማለፍ አልቻሉም።


 

በሌላኛው ጨዋታ ስዊድን ፖላንድን 3 ለ 2 አሸንፋለች።

በስትሮውበሪ አሬና ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አንቶኒ ኢላንጋ፣ ጉስታፍ ላገርቢልክ እና ቪክቶር ዮኮሬሽ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

የአርሰናሉ አጥቂ ዮኮሬሽ በ88ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ግብ ስዊድንን ለዓለም ዋንጫ አሳልፏታል።

ኒኮላ ዛሌውስኪ እና ካሮል ስዊዴርስኪ ለፖላንድ ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።


 

በፋዲል ቮክሪ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ቱርክዬ ኮሶቮን 1 ለ 0 አሸንፋለች።

ኬረም አክቱርኮግሉ ግቧን ከመረብ ጋር አገናኝቷል።

ቼክ ሪፐብሊክ ዴንማርክን በመለያ ምት 3 ለ 1 አሸንፋለች።

ሁለቱ ቡድኖች በ12ዐ ደቂቃ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።

በኢፒኢቲ አሬና ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፓቬል ሱልች እና ላዲስላቭ ክሬጄቺ ለቼክ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ዮአኪም አንደርሰን እና ካስፐር ዋርትስ ሆግ ለዴንማርክ ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ጨዋታው በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአቻ በመጠናቀቁ ምክንያት ወደ ጭማሪ ሰዓት አምርቷል።

ላዲስላቭ ክሬጄቺ ለቼክ፣ ዋርትስ ሆግ በጭማሪ ሰዓት ግብ አስቆጥረዋል።

ቡድኖቹ ወደ መለያ ምት አምርተው ቼክ ሪፐብሊክ 3 ለ 1 በማሸነፍ ለዓለም ዋንጫ አልፋለች።

ውጤቱን ተከትሎ ስዊድን፣ቱርክዬ፣ቼክ ሪፐብሊክ እና ቦሲኒያና ሄርዞጎቪና ለ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ አልፈዋል።

አራቱ ሀገራት አስቀድመው በቀጥታ ወደ ዓለም ዋንጫ ያለፉ 12 የአውሮፓ ሀገራት ተቀላቅለዋል።

አውሮፓ በዓለም ዋንጫው 16 ሀገራትን ታሳትፋለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም