ቀጥታ፡

ኢራቅ ከ40 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫ ተመልሳለች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የክፍለ አህጉራት የፍጻሜ ማጣሪያ ኢራቅ ቦሊቪያን 2 ለ 1 አሸንፋለች።

ዛሬ ማለዳ ላይ በሜክሲኮ በቢቢቪኤ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ አሊ አል ሃማዲ እና አይማን ሁሴን የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ሞሰስ ፓኒያጉዋ ለቦሊቪያ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

በጨዋታው ቦሊቪያ የተሻለ ብልጫ የነበራት ቢሆንም ኢራቅ ከፈጠረቻቸው ሶስት ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች መካከል ሁለቱን ወደ ግብ በመቀየር ውጤታማ ሆናለች።

ግብ ያስቆጠረው የኢራቁ አይማን ሁሴን የጨዋታው ኮከብ በመባል ተመርጧል።

ኢራቅ ከ40 ዓመታት በኋላ ለዓለም ዋንጫ አልፋለች።

የሜሶፖታሚያ አንበሶች ለመጨረሻ ጊዜ በውድድሩ ላይ የተሳተፉት እ.አ.አ በ1986 ሜክሲኮ ባዘጋጀችው 11ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ነበር።

ኢራቅ በውድድሩ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ትሳተፋለች።

ቦሊቪያ ከ32 ዓመታት በኋላ ለዓለም ዋንጫ የማለፍ ህልሟ አልተሳካም።

ለመጨረሻ በውድድሩ ላይ የተሳተፈችው እ.አ.አ በ1994 በአሜሪካ በተዘጋጀው 15ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ላይ ነው።

ትናንት ከእኩለ ሌሊት በኋላ በሜክሲኮ አክሮን ስታዲየም በተካሄደው የክፍለ አህጉራት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጃማይካን 1 ለ 0 በማሸነፍ ከ52 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ትልቁ የእግር ኳስ መድረክ ተመልሳለች።

በአውሮፓ ትናንት ማምሻውን የተካሄዱ የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ተከትሎ ስዊድን፣ ቱርኪዬ፣ ቼክ ሪፐብሊክ እና ቦሲኒያና ሄርዞጎቪና ለዓለም ዋንጫ አልፈዋል።

ጣልያን በመለያ ምት ተሸንፋ ከ12 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫ የመመለስ ህልሟ ተጨናግፏል።

ጨዋታዎቹን ተከትሎ ለዓለም ዋንጫ ያለፉ ሀገራት ሙሉ ለሙሉ ተለይተዋል።


 

23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ከሰኔ 4 እስከ ሐምሌ 12 ቀን 2018 ዓ.ም በአሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ ጣምራ አዘጋጅነት ይካሄዳል።

በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ሀገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም