በሀገራዊ ለውጡ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና የቀጣናውን ሰላም የሚያስጠብቅ አስተማማኝ ሠራዊት ተገንብቷል - ኢዜአ አማርኛ
በሀገራዊ ለውጡ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና የቀጣናውን ሰላም የሚያስጠብቅ አስተማማኝ ሠራዊት ተገንብቷል
አዲስ አበባ፤መጋቢት 22/2018(ኢዜአ)፦በሀገራዊ ለውጡ የኢትዮጵያን ክብርና ብሔራዊ ጥቅም እንዲሁም የቀጣናውን ሰላም የሚያስጠብቅ አስተማማኝ ሠራዊት መገንባቱን የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገለጹ።
የመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት የለውጡ መንግሥት ተቋማዊ ግንባታን የሀገረ መንግሥት ግንባታ ዋና ምሰሶ አድርጓል።
በዚህም ጠንካራና አስተማማኝ የጸጥታና ደህንነት ተቋማትን መገንባት ከሀገራዊ የሪፎርም አምዶች መካከል አንዱ በማድረግ ስኬታማ ተግባራትን አከናውኗል።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሁሉም ተቋማዊ አውዶች ሰፊ ሪፎርም አድርጓል።
ከየትኛውም አቅጣጫ የሚቃጣ ጥቃትን የሚመክት ብቁ የምድር ኃይል፣የአየር ኃይል፣ የሜካናይዝድ፣የባሕር ኃይል፣ የልዩ ዘመቻ እና የሳይበር ኃይል መገንባቱንም ነው ያነሱት።
የሀገር ኩራት የሆነ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በመገንባት ረገድ በሰው ሃይል፣በአደረጃጀትና በውጊያ ቴክኖሎጂ የላቀ የለውጥ ሥራ በማከናወን ጠንካራ ተቋማዊ ቁመና መፈጠሩንም ገልጸዋል።
ሀገራዊ ለውጡ ኢትዮጵያ ግዳጁን በላቀ ብቃት የሚወጣና ጦርነትን በሩቁ የሚቀለብስ አስተማማኝ ሠራዊት እንዲኖራት አስችሏል ነው ያሉት።
መከላከያን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከማስታጠቅ ባለፈ፣ ዓለም የደረሰበትን የውጊያ ቴክኖሎጂ የሚጠቀምና በአግባቡ የሚመራ ብቁ የሰው ኃይልን የማብቃት ሥራዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በወታደራዊ መሣሪያዎች ራስን ለመቻል የተያዘውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካትም፣ የመከላከያ ኢንዱስትሪ ተቋማት ላይ ስኬታማ ሪፎርም በማድረግ ወደ ተጨባጭ ውጤት እንዲመጡ ተደርጓል ነው ያሉት።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተሰማራበት ቦታ ሁሉ የሰላም ማስከበር ግዳጆችን በብቃት በመወጣት በቀጣናው ተፈላጊ ሠራዊት መሆኑን በተግባር አስመስክሯል።
ለቀጣናው ሠላም መረጋጋት የኢትዮጵያ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ያረጋገጠ ውጤት አስመዝግቧል ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የደህንነት እና ሰላም ችግሮች በአፍሪካውያን እንደሚፈቱ ጽኑ እምነት አላት ያሉት ሚኒስትሯ፤ ለዚህም አፍሪካውያን የሰላምና ደህንነት ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ እየሠራች ነው ብለዋል።
ከበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ጋር በመከላከያ ጉዳዮች በትብብር ለመሥራት ስምምነቶች መደረጋቸውን በመጠቆም፥ኢትዮጵያ ልምዷን ለማካፈልና አጋርነቷን ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በአቅም፣በዲሲፕሊን፣ በስነ ልቦና እና በአስተሳሰብ ከየትኛውም ወገንተኝነት የጸዳ ኢትዮጵያዊ ሠራዊት መገንባቱንም ሚኒስትሯ አንስተዋል።
በዚህም ሠራዊቱ ከማንኛውም የፖለቲካ ተጽዕኖ ነፃ ሆኖ ለሕገ-መንግሥቱና ለሀገር ሉዓላዊነት ብቻ የሚቆምበት መሠረት ተጥሏል።