ሮቤርቶ ዴ ዘርቢ የቶተንሃም ሆትስፐርስ አሰልጣኝ ሆነው ተሾሙ - ኢዜአ አማርኛ
ሮቤርቶ ዴ ዘርቢ የቶተንሃም ሆትስፐርስ አሰልጣኝ ሆነው ተሾሙ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2018 (ኢዜአ)፦ ቶተንሃም ሆትስፐር ጣልያናዊውን አሰልጣኝ ሮቤርቶ ዴ ዘርቢን በአምስት ዓመት ኮንትራት አዲሱ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙን ዛሬ ይፋ አድርጓል።
ክለቡ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው የቀድሞው ጊዜያዊ አሰልጣኝ ኢጎር ቱዶር በቆይታቸው ደካማ ውጤት በማስመዝገባቸውና ክለቡን ለወራጅ ቀጠና ስጋት ይበልጥ ማጋለጣቸውን ተከትሎ መሆኑን ስካይ ስፖርትስ ዘግቧል።
የ46 ዓመቱ አሰልጣኝ ዴ ዘርቢ ከክለቡ አመራሮች ጋር ባደረጉት ስምምነት መሰረት እስከ 2031 ድረስ በለንደኑ ክለብ ለመቆየት ፊርማቸውን አኑረዋል።
ዴ ዘርቢ ክለቡን በአሰልጣኝነት የተረከቡት ከፈርንሳዩ ማርሴይ ጋር በጋራ ስምምነት መለያየታቸውን ተከትሎ ነው።
በውላቸው ላይ ክለቡ ወደ ታችኛው ሊግ ቢወርድ እንኳ ኮንትራቱን የሚያቋርጥ አንቀጽ (relegation clause) አለማካተቱ፣ በአሰልጣኙ ላይ ያለውን የረጅም ጊዜ እምነት እንደሚያሳይ ተገልጿል።
ዴ ዘርቢ የክለቡ አሰልጣኝ ከሆኑ በኋላ በሰጡት መግለጫ ቶተንሃምን የመሰለ ታላቅ ክለብ በመቀላቀላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የክለቡ አመራሮች ያላቸው የወደፊት ራዕይ እና የሚከተሉት የማጥቃት እግር ኳስ ፍልስፍና ወደ ክለቡ እንዲመጡ እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።
አሰልጣኙ ደጋፊዎችን የሚያስደስት ጨዋታ ለማሳየት ቃል ገብተዋል።
የአሰልጣኙ አፋጣኝ እና ቀዳሚ ተግባር ቶተንሃም በዘንድሮው የውድድር ዘመን በፕሪምየር ሊጉ እንዲቆይ ማድረግ ነው።
ቶተንሃም ሆትስፐርስ በ30 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዟል። 18ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ዌስትሃም ዩናይትድ የሚበልጠው በአንድ ነጥብ ነው።
ክለቡ ባለፉት 13 የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። ቀሪዎቹ ሰባት ጨዋታዎች ለአሰልጣኙ ትልቅ ፈተና እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
ሮቤርቶ ዴ ዘርቢ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ሚያዝያ 4 ቀን 2018 ዓ.ም ከሰንደርላንድ ጋር በ32ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነው።
እስከ ውድድር ዘመኑ ፍጻሜ ድረስ ክለቡን በደረጃ ሰንጠረዡ ከፍ ለማድረግ በሙሉ ትኩረት እና ትጋት እንደሚሰሩ አሰልጣኝ ዴ ዘርቢ አመልክተዋል።