በጠንካራ የጥገና፣እድሳትና ኦፕሬሽን አገልግሎት ስኬታማ አየር መንገድ መፍጠር ተችሏል- ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው - ኢዜአ አማርኛ
በጠንካራ የጥገና፣እድሳትና ኦፕሬሽን አገልግሎት ስኬታማ አየር መንገድ መፍጠር ተችሏል- ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው
አዲስ አበባ፤መጋቢት 22/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በጠንካራ የጥገና፣ እድሳትና ኦፕሬሽን አገልግሎት ስኬታማ አየር መንገድ መፍጠር መቻሏን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
በአዲስ አበባ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ የጥገና፣ ዕድሳትና ኦፕሬሽን ኮንፍረንስ 2026 ዛሬ ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ የተሟላ የጥገና፣ እድሳትና ኦፕሬሽን አገልግሎት ስኬታማ አየር መንገድ መገንባት ያስችላል።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ የጥገና፣ ዕድሳትና ኦፕሬሽን አገልግሎት ለብዙ ዓመታት ሰርቻለሁ ያሉት አቶ መስፍን ዘርፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስኬት ቁልፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስኬት ምስጢር በአየር መንገዱ ያለው የተሟላ የጥገና፣ ዕድሳትና ኦፕሬሽን አገልግሎት መሆኑን ተናግረዋል።
በአፍሪካ የጥገና፣ዕድሳትና ኦፕሬሽን አገልግሎት ክፍተት ያለበት በመሆኑ የአየር መንገዶችም ደካማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአፍሪካ ጠንካራ የጥገና፣ዕድሳትና ኦፕሬሽን አገልግሎት ለመስጠት ሰፊ ሀብትና ዕውቀት ይፈልጋል ያሉት አቶ መስፍን፤ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የአፍሪካ አየር መንገዶች በትብብር መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
አፍሪካ ዕምቅ አቅም ያላቸው ወጣቶች እንዳሏት ገልጸው፤ወጣቶችን አሰልጥኖ ማሰማራት ይገባል ብለዋል።
በተለያዩ ዓለማት ካሉ የአየር መንገድ የጥገና፣ዕድሳትና ኦፕሬሽን ተቋማት ጋር በጋራ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።