ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ወደ ምድብ ማጣሪያው አለፈች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2018 (ኢዜአ)፦ በ36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ኢትዮጵያ ሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔን 1 ለ 0 አሸንፋለች።

በድሬዳዋ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቸርነት ጉግሳ በሰባተኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ዋልያዎቹ በጨዋታው ላይ በኳስ ቁጥጥር እና የግብ እድሎችን በመፍጠር የተሻሉ ነበሩ።

ከእረፍት መልስ ቸርነት ጉግሳ ያልተጠቀመባት ግልጽ የግብ እድል በጨዋታው ተጠቃሽ ከሚባሉ ክስተቶች መካከል አንዱ ነው።

በርካታ ደጋፊዎች በድሬዳዋ ስታዲየም በመገኘት ጨዋታውን ተከታትለውታል።

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ በድምር ውጤት በማሸነፍ በ36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ወደ ምድብ ድልድል ማለፏን አረጋግጣለች።

ብሔራዊ ቡድኑ በመጀመሪያው ጨዋታ 3 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የ36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ከመስከረም እስከ ህዳር ወር 2019 ዓ.ም ይካሄዳል።

36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እ.አ.አ በ2027 በታንዛንያ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ ጣምራ አዘጋጅነት ይካሄዳል።

በውድድሩ ላይ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም