በቀጣዮቹ ጊዜያት የቤት አቅርቦት ፍላጎትን በዘላቂነት ለመመለስ በትኩረት ይሰራል-ረሻድ ከማል (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣዮቹ ጊዜያት የቤት አቅርቦት ፍላጎትን በዘላቂነት ለመመለስ በትኩረት ይሰራል-ረሻድ ከማል (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤መጋቢት 22/2018 (ኢዜአ)፦በቀጣዮቹ ጊዜያት የቤት አቅርቦት ፍላጎትን በዘላቂነት ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰራ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል (ዶ/ር) ገለጹ።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ምስረታ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ላለፉት ሶስት ቀናት "በአዲስ ምዕራፍ ለተሻለ ነገ" በሚል መሪ ሀሳብ ሲካሄድ ቆይቷል።
በመርሀ ግብሩ በኮርፖሬሽኑ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ ህንጻዎች የተመረቁ ሲሆን፤ሀገራዊ ለውጡን መነሻ አድርጎ በተቋማዊ ሪፎርሙ የተመዘገበውን ስኬት የሚያስቃኝ ኤግዚቢሽን ለዕይታ ክፍት ሆኖ ቆይቷል።
በዛሬው ዕለትም የበዓሉ የማጠቃለያ መድረክ የተካሄደ ሲሆን፤ለተቋሙ ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም እውቅና ተሰጥቷል።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የበዓሉ ዓላማ በባለፉት ዓመታት የተገኙ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል እና ከክፍተቶችም ትምህርት ለመውሰድ ነው።
ተቋሙ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ስኬታማ ጉዞ ማድረጉን ገልጸው፤ በተቋሙ የተከናወነው የሪፎርም ስራ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቁመዋል።
ተቋሙ ባለፉት ሀምሳ ዓመታት በበርካታ ውጣ ውረዶች ማለፉን ገልጸው፤ ኮርፖሬሽኑ አሁን ላለበት ስኬት የላቀ አስተዋጽኦ የነበራቸውን አካላት አመስግነዋል።
በቀጣይም በርካታ ስራዎች በእቅድ መያዛቸውን ገልጸው፤ የቤት አቅርቦት ፍላጎትን በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽኑ ለሰው ልጅ መሰረታዊ በሆነው የቤት ፍላጎት ላይ እንደሚሰራ ገልጸው፤ ባለድርሻ አካላት ከኮርፖሬሽኑ ጋር በቅርበት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።