ቀጥታ፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሠላም እሴት ግንባታ  ያላቸውን ሚና ማጠናከር አለባቸው

አሶሳ፤ መጋቢት 22/2018 (ኢዜአ)፦ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሠላም እሴት ግንባታ ያላቸውን ሚና ማጠናከር እንዳለባቸው ተመላከተ።

“ሠላም እና አካታች ልማትን ለማረጋገጥ የምሁራን ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ  ለአራተኛ ጊዜ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የምሁራን ጉባኤ  ተካሄዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ እንደተናገሩት፤  ዩኒቨርሲቲዎች ከመማር ማስተማር ስራቸው ባለፈ የህዝቦችን ትስስር በሚያጠናክሩና ሰላምን በሚያፀኑ ተግባራት ላይ   ማተኮር አለባቸው።


 

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሠላም እሴት ግንባታ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የተጠናከሩ ስራዎችን ማከናወን እንዳለባቸውም ነው ያሳሰቡት።

ዩኒቨርሲቲው የሚያካሄዳቸው ማህበረሰብ ተኮር የምርምር ስራዎች ለክልሉ ልማት እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተጨማሪ አቅም እየፈጠሩ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ከማል አብዱራሂም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው የዕውቀት መፍለቂያ እና የምርምር ተቋም ከመሆን ባሻገር ለሰላም መስፈን የድርሻውን እየተወጣ ነው ብለዋል።

በተለይ በሠላም ግንባታ፣ በልማት እና ተያያዥ ጉዳዮች የሚያደርገውን ጥናትና ምርምር ወደ ተግባር በመቀየር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በመድረኩ ላይ በዩኒቨርሲቲው ምሁራን ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አስካለች አልቦሮን ጨምሮ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ የስራ ኃላፊዎችና ምሁራን ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም