ቀጥታ፡

የቱሪዝም ዘርፉ ኢኮኖሚ እንዲያመነጭ ለማስቻል ለሰላም ትኩረት መስጠት ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

ሀረር፣መጋቢት 22/2018(ኢዜአ):-የቱሪዝም ዘርፉ ኢኮኖሚ እንዲያመነጭ በማስቻል የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሰላም ትኩረት መስጠት ይገባል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።

የሰላም ሚኒስቴር ''የሰላም ቱሪዝም ለሀገር ግንባታ'' በሚል መሪ ቃል ለማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች በሀረር ከተማ የምክክር እና ጉብኝት መርሀ-ግብር እያካሄደ ነው።


 

መርሀ-ግብሩ በአካባቢው ያሉ የቱሪስት መስህቦች እና ታሪካዊ ስፍራዎችን በማስጎብኘት የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪዎች ለሀገር ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ነው።

አቶ ኦርዲን በድሪ በመርሀ-ግብሩ ላይ እንደገለፁት፥ የሀረር ከተማ የተለያዩ እምነት፣ባህልና ቋንቋ ያላቸው ብሄር ብሄረሰቦች በአንድነት የሚኖሩባት የሰላም ተምሳሌት ከተማ ናት።

በተለይ በአጭር ርቀት ውስጥ የተለያዩ ቤተ እምነቶች አንዱ ለሌላኛው ስጋት ሳይሆኑ ማህበረሰቡም በሰላምና አብሮነት ተማምነው የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን ገልፀዋል።

ሁለት ቅርሶችን በአለም አቀፍ ቅርስነት ያስመዘገበች በተለይ ኢኮኖሚ በማመንጨት የክልሉን ዕድገት ለማፋጠን የሚያስችሉ የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በጉያዋ አቅፋ የምትገኝ ከተማ መሆኗንም ጠቁመዋል።

በተለይ ከ5 መቶ አመታት በፊት አለም አቀፉን የጁገል ቅርስ ማህበረሰቡን አስተባብሮ መገንባት መቻሉ በወቅቱ የነበረውን የምዕናብ ከፍታ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ሆኖም በውስጧ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በአግባቡ አልምቶ ለመጠቀም ሰላም ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን አክለዋል።

መሰል መርሀ-ግብሮችም ቅርሶችን ለማስተዋወቅና ለሰላም እሴት ግንባታ አበርክቷቸው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይ ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን በማስቻል ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም