ቀጥታ፡

ፈተናን ወደ ዕድል የቀየረ የዲፕሎማሲ ከፍታ!!!

የኢትዮጵያ መንግሥት ላለፉት ስምንት ዓመታት የተከተለው ንቁና ስልታዊ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ የሀገራችንን የውጭ ግንኙነት ለዘመናት በተዛባ መልኩ ይዞት ከነበረው “በጠላቶች የመከበብ እይታ” በማላቀቅ ለላቀ ዓለም አቀፋዊ ከፍታ የሚመጥን መሠረት ጥሏል።

የለውጡ መንግሥት የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ዋነኛ መለኪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ነው። ሀገራችን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የራሷን የሉዓላዊነትና የልማት ፍላጎት ማዕከል ያደረገ የውጭ ግንኙነት መርህን ስትከተል ቆይታለች።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ያጋጠሙንን ዓለም አቀፍ ጫናዎች በብቃት በመቋቋም እና የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነቶችን በማጠናከር እንደ BRICS አባልነት ያሉ የሀገራዊ ክብራችን ማሳያ የሆኑ ስኬቶችን አስመዝግበናል ይህ ውጤት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነትና የውሳኔ ሰጪነት ዐቅም በተግባር ያረጋገጠ ነው።

“ቅድሚያ ለጎረቤት የሚለው መርህ ከቃላት ባለፈ በተግባራዊ ዲፕሎማሲ በመተርጎሙ ቀጣናዊ ግንኙነታችን ከጥርጣሬ አጥር ወጥቶ ወደ ጽኑ ስልታዊ አጋርነት ተሸጋግሯል። ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የትስስር ማዕከል በመሆን በታዳሽ ኃይል ፣ በመንገድ፣ በመጠጥ ዉሃ እና በባቡር መሠረተ ልማቶች የቀጣናውን ሀገራት ዕጣ-ፈንታ ከራሷ ጋር አስተሳስራለች።

ይህ የጋራ ዕድገት ስትራቴጂ ኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ምሰሶ ብቻ ሳይሆን፣ የማይበገርና መሪ ቀጣናዊ ኃይል እንድትሆን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡

“ዜጋ ተኮር” የዲፕሎማሲ አቅጣጫችን የመንግሥታችን ሕዝባዊ ወገንተኝነትና ጽኑ ቁርጠኝነት መገለጫ ነው።

ዜጎች ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ በሕጋዊ መንገድ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሰብዓዊ መብታቸው የማይጠበቅበት ሁኔታ ተፈጥሮ ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ዜጎችን ወደ እናት ሀገራቸው ለመመለስ የተከናወኑ ተግባራት መንግሥት ለሕዝቡ ያለውን አለኝታነት ያሳዩና በዜጎች ዘንድ የላቀ ብሔራዊ ኩራትና መተማመንን የፈጠሩ ታሪካዊ ክስተቶች ናቸው።

በአለም ዲፕሎማሲያዊ መድረኮች ተፅዕኖዋ እየጎላ እና ጥንካሬዋ እየጎለበተ የመጣው ሀገራችን አሁንም የፓን አፍሪካኒዝም ማማና የፅናት ተምሳሌት መሆኗን ለዓለም በዳግሚ ያረጋገጠ የታሪክ ምዕራፍ ተገኝታለች።

ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት ስልታዊ የዲፕሎማሲ ድሎች የኢትዮጵያን ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ወደ ላቀ ከፍታ አሸጋግረውታል። ዛሬ ሀገራችን በውጭ ግንኙነቷ የምትታወቀው የቀጠናዊ አጀንዳዎች ምንጭና የመፍትሔ አካል በመሆን ነው።

ይህ አዲስ ገጽታችንና እየተገነባ ያለው ብሔራዊ ኩራት ለሚገጥሙን ተግዳሮቶች እንዳንበረከክ አቅምና የልማት ጉልበት ሆኖልናል።

በዚህ ተለዋዋጭ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ በሳል፣ በስትራቴጂ የሚመራና ብሔራዊ ጥቅም ላይ ያነጣጣረ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ስራችን ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዜጎች በሁሉም መስክ የሃገራቸው አምባሳደር በመሆን የድርሻቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉና መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

የኢፌድሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

መጋቢት 22 /2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም