ባለፉት የለውጥ ዓመታት የወል ትርክትን ለመገንባትና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የወል ትርክትን ለመገንባትና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል
አርባምንጭ፤ መጋቢት 22/2018(ኢዜአ)፦ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሀገሪቱ የወል ትርክትን ለመገንባትና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መመዝገቡን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሠ ጫፎ ገለጹ።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በጋሞ ዞን ለህዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩ የብልጽግና ፓርቲ ዕጩዎችን የማስተዋወቅ መርሃ-ግብር ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።
የህዝቡን አንድነትና ወንድማማችነት በማጠናከር በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ ዘርፎች ሊቆጠሩ የሚችሉ ስኬቶች ተመዝግበዋልም ብለዋል።
ብሔራዊ ጥቅምን በማስከበርና የህዝቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውንም አፈ-ጉባኤው ተናግረዋል።
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እንደ ሀገር የተያዙ ትልሞችን በማሳካት ኢትዮጵያን የተምሳሌት ሀገር ለማድረግ እንደሚሰራም አመልክተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው በመደመር እሳቤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ራዕይ ሰንቀን እየሠራን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም አመራሩና ህዝቡ በቅንጅት እየተጋ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ሰፊ የመልማት አቅም ያለ በመሆኑ ፀጋዎችን ወደ ሀብት በመቀየር የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ቅቡልነት ያለው እንዲሆን የክልሉ መንግስት አበክሮ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው ህዝቡም ለምርጫው ስኬት የበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ(ዶ/ር) የዞኑ ህዝብ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፎች ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ድሎች ተመዝግበዋል ብለዋል።
የጸና ሰላም፣ አንድነትና ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ከህዝቡ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።