ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት በምርምር ማገዝ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት በምርምር ማገዝ ይገባል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በምርምርና በሳይንስ ማገዝ እንዳለባቸው የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ገለፁ።
የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የአየር ንብረት ትግበራ ፎረም የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን በዚሁ ወቅት፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚደረገው ብሔራዊ ጥረት ሊኖራቸው የሚገባውን ስትራቴጂያዊ ሚና አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ሳይንሳዊ የመፍትሄ ሃሳቦችን በማፍለቅ በኩል በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አቶ ስዩም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመመከት በአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን በመተግበር ቀዳሚ መሆኗን ጠቁመዋል።
ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን መትከል እና በታዳሽ ኃይል ልማት የተመዘገቡት ስኬቶች ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለዓለም አርአያ መሆኗን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጥናትና ምርምር ስራዎቻቸው፣ የድህረ-ምረቃ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሁፎችንና ጆርናሎቻቸውን በአየር ንብረት ለውጥና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መሆን አለባቸው ብለዋል።
ፎረሙ የፖሊሲ አውጪውንና የትምህርት ተቋማቱን የተቀናጀ ስራ የሚያጠናክር መድረክ እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የአየር ንብረት ጉዳዮችን በበላይነት እንደሚመራ ተቋም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የጀመረውን ቅንጅት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲዎች የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችሉ ሳይንሳዊ መፍትሄዎችን በማፍለቅ በኩል ከፍተኛ ሚና አላቸው።
እንደሀገር እየተተገበረ ባለው የአረንጓዴ አሻራ ልማት እና የአየር ንብረት መቋቋም አቅም ግንባታ ስራዎች ላይ የዩኒቨርሲቲዎች ተሳትፎ ከንድፈ ሀሳብ ወደ ተግባር የተሻገረ መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል።
የፎረሙ መመስረት ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ ፍለጋ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸው እንደሀገር የተጀመሩ ሥራዎችን መደገፍ የሚያስችል ነው ብለዋል።