የምርጫ ሥርዓት የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጥ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ መሳሪያ ነው - ፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
የምርጫ ሥርዓት የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጥ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ መሳሪያ ነው - ፖለቲካ ፓርቲዎች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2018 (ኢዜአ)፦የምርጫ ሥርዓት የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት በተግባር የሚያረጋግጥ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ መሳሪያ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ድምፅ በሚሰጥበት የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28/2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህም "በምርጫዬ" መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት እስከ መጋቢት 18/2018 ዓ.ም ድረስ በአጠቃላይ ከ28 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ መራጮች መመዝገባቸውን ቦርዱ አስታውቋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫም 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ የመገናኛ ብዙኅን አማራጮችን በመጠቀም የፖሊሲ ሃሳባቸውን ለህዝብ እያቀረቡ ይገኛል።
የምርጫ ሂደቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተፎካካሪ የሚያደርጋቸውን ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአዲሱ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዝዳንትና የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን ታፈሰ፤ ምርጫ የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት የሚረጋገጥበት ዴሞክራሲያዊ ሂደት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የዕጩዎችና መራጮች ምዝገባ በዲጂታል ሥርዓት ጭምር በማድረግ አስቻይ የምርጫ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
ለዚህም በመጪው ግንቦት ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊነትን ለማስጠበቅ የበኩላቸውን አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት በማጠናቀቅ በሂደቱ ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
የቁጫ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ባንዲራ በላቸው በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ምቹና አሳታፊ የፉክክር ምኅዳር መፍጠሩን አንስተዋል።
በዚህም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሃሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ የምርጫ ፉክክር በማድረግ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የአንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጸሐፊና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መምህር ሰለሞን አኒባል፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ ለፓርቲያቸው ምስረታ ሰፊ የፖለቲካ ምኅዳር መፍጠሩን ገልጸዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት በማረጋገጥ የሰለጠነ የፖለቲካ ሽግግር የሚደረግበት ወሳኝ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።
የምርጫ ሥርዓት የህዝብ የስልጣን ባለቤትነትን የሚያረጋግጥ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ መሳሪያ ነው ያሉት ኃላፊው፤ በምርጫ ሂደትም የሀገር ብሔራዊ ጥቅምና የህዝብ አንድነት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።
መገናኛ ብዙኅን የሚዘጋጁ የክርክር መድረኮችም የፓርቲዎችን የፖሊሲ አማራጮች ከህዝብ ጋር በማገናኘት ለትውልድ የሚተርፍ የዴሞክራሲ ልምምድና አሻራ እያኖሩ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም የመገናኛ ብዙኅን የክርክር መድረኮችን ህዝብና ሀገርን በሚያሻግሩ በሳል የፖሊሲ ሃሳቦችን ለህዝብ በማቅረብ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።