ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታዋን ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር ታደርጋለች 

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታዋን ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር ዛሬ ያከናውናል።

የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ በድሬዳዋ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።

ሀገራቱ መጋቢት 18 ቀን 2018 ዓ.ም በሞሮኮ ኤል አብዲ ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ 3 ለ 0 ማሸነፏ ይታወቃል።

አቤል ያለው ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ከነዓን ማርክነህ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ውጤቱን ተከትሎ በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመሩት ዋልያዎቹ ወደ ምድብ ድልድል የመግባት እድላቸውን አስፍተዋል።

ብሔራዊ ቡድኑ ለመልሱ ጨዋታ ዝግጅት መጋቢት 20 ቀን 2018 ዓ.ም ድሬዳዋ የደረሰ ሲሆን የመጨረሻ ልምምዱን ጨዋታው በሚካሄድበት ድሬዳዋ ስታዲየም ትናንት ማምሻውን አድርጓል።

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከጨዋታው በፊት ትናንት በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ላይ ባገኘው ድል ሳይዘነጋ የመልሱን ጨዋታ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ገልጸዋል።

አሰልጣኙ ቢኒያም አይተን በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከቢኒያም ውጪ ሁሉም ተጫዋቾች በሙሉ በጤንነት ላይ መሆናቸውን አንስተዋል።

በአባቱ ድንገተኛ ህልፈት ምክንያት በመጀመሪያው ጨዋታ ያልነበረው የቡድኑ አምበል ጋቶች ፓኖም ለመልሱ ጨዋታ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በመቀላቀል ልምምድ ማድረጉን አመልክተዋል። 

በ47 ዓመቱ ፓርቹጋላዊ ሪካርዶ ሞናሳንቶ የሚመራው የሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታውን ለማድረግ ከትናንት በስቲያ ድሬዳዋ መግባቱ ይታወቃል። 

የመጨረሻ ልምምዱንም ትናንት በድሬዳዋ ስታዲየም ሰርቷል።

ካፍ የነገው የኢትዮጵያ እና ሳኦቶሜ ጨዋታ በዝግ እንዲካሄድ ውሳኔ አሳልፎ ነበር።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በስታዲየሙ ዙሪያ የተሰጡ የግምገማ አስተያየቶችን መሰረት በማድረግ በፍጥነት ለማስተካከል እርምጃ ወስዷል። 

የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ከከተማ አስተዳደሩ እርምጃ ጎን ለጎን ጨዋታው ለተመልካች ክፍት እንዲሆን ባደረገው ከፍተኛ ጥረት እንዲሁም የካፍ ሴኪዩሪቲ ኦፊሰር በአካል ተገኝተው ከገመገሙ በኋላ በላኩት ሪፖርት መሰረት ካፍ 10 ሺህ ተመልካች በስታዲየም ተገኝቶ እንዲከታተል ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈች ወደ ምድብ ድልድል ምዕራፍ ማለፏን ታረጋግጣለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም