ቀጥታ፡

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከ52 ዓመታት በኋላ ለዓለም ዋንጫ ታልፍ ይሆን?   

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2018(ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የሚሳተፉ ቀሪ ሀገራት የሚለዩባቸው የመጨረሻ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች የተመልካቾችን ትኩረት ስበዋል።

በዓለም ዋንጫው የክፍለ አህጉራት የፍጻሜ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። 

አፍሪካዊቷ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከጃማይካ ጋር ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት በሜክሲኮ አክሮን ስታዲየም ይጫወታሉ።

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በፊፋ የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ የተሻለ ደረጃ (48ኛ) በመያዟ ቀጥታ ለዛሬው የፍጻሜ ጨዋታ አልፋለች።

ጃማይካ በግማሽ ፍጻሜው ኒው ካሌዶኒያን 1 ለ 0 አሸንፋለች።

የማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ሀገር ለመጨረሻ ጊዜ በውድድሩ ላይ የተሳተፈችው እ.አ.አ በ1974 በጀርመን (በወቅቱ አጠራሯ ምዕራብ ጀርመን) አስተናጋጅነት በተካሄደው 10ኛው የዓለም ዋንጫ ነው።

ውድድሩ የሀገሪቷ ብቸኛ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ነው። 

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ካሸነፈች ከ52 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫ በማለፍ ታሪክ የመስራት እድል ታገኛለች።

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የምትሳተፍ 10ኛ የአፍሪካ ሀገር ትሆናለች።

ሞሮኮ፣ ሴኔጋል፣ ግብጽ፣ ኮትዲቯር፣ አልጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና እና ኬፕ ቨርዴ ለዓለም ዋንጫ ያለፉ የአፍሪካ ሀገራት ናቸው።

በሌላኛው መርሐ ግብር ቦሊቪያ ከኢራቅ ነገ ማለዳ 12 ሰዓት ላይ በቢቢቪኤ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ኢራቅ ኮንጎ በፊፋ የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ የተሻለ ደረጃ (55ኛ) በመያዟ ለጥሎ ማለፍ የፍጻሜ ጨዋታው በቀጥታ አልፋለች።

ቦሊቪያ በግማሽ ፍጻሜ ማጣሪያው ሱሪናምን 2 ለ 1 በማሸነፍ ለወሳኙ ጨዋታ ደርሳለች።

አሸናፊ ሀገራት ለዓለም ዋንጫው ያልፋሉ። 

በተያያዘም የዓለም ዋንጫ የአውሮፓ ዞን የጥሎ ማለፍ የፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።

ቦሲኒያ እና ሄርዞጎቪና ከጣልያን ጋር ምሽት 3 ሰዓት ከ45 ላይ በቢሊኖ ፖልጄ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የአራት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ጣልያን ከ12 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫው ለመመለስ የምታደርገው ጨዋታ ትኩረት ስቧል። 

አዙሪዎቹ ለመጨረሻ ጊዜ በውድድሩ ላይ የተሳተፉት እ.አ.አ በ2014 ብራዚል ባዘጋጀችው 20ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ነው።

ጣልያን ባለፉት ሁለት የዓለም ዋንጫዎች አለመሳተፏ በዓለም እግር ኳስ ውስጥ ትልቅ መነጋገሪያ የሆነ ጉዳይ ነው። 

በ48 ዓመቱ ጄናሮ ጋቱሱ የሚመራው የጣልያን ብሔራዊ ቡድን ወደ ዓለም ዋንጫው የሚያሳልፋትን ትኬት ለመቁረጥ ቦስኒያን መርታት ይጠበቅበታል።
በሌሎች መርሐ ግብሮች ስዊድን ከፖላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክ ከዴንማርክ እና ኮሶቮ ከቱርኪዬ በተመሳሳይ ምሽት 3 ሰዓት ከ45 ላይ ይጫወታሉ።

በጥሎ ማለፉ የሚያሸንፉ አራት ሀገራት አስቀድመው በቀጥታ ወደ ዓለም ዋንጫ ያለፉ 12 የአውሮፓ ሀገራትን ይቀላቀላሉ።

አውሮፓ በ23ኛው የዓለም ዋንጫ 16 ሀገራትን ተሳትፋለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም