ቀጥታ፡

ካፍ የኢትዮጵያ እና የሳኦቶሜና ፕሪንሲፔ ጨዋታን 10 ሺህ ተመልካች ስታዲየም ተገኝቶ እንዲከታተለው ወሰነ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሳኦቶሜና ፕሪንሲፔ አቻው ጋር የሚያደርገውን የ36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ 10 ሺህ ተመልካች በድሬዳዋ ስታዲየም ተገኘቶ እንዲከታተለው መወሰኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ካፍ የነገው የኢትዮጵያ እና ሳኦቶሜ ጨዋታ በዝግ እንዲካሄድ ውሳኔ አሳልፎ ነበር።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በስታዲየሙ ዙሪያ የተሰጡ የግምገማ አስተያየቶችን መሰረት በማድረግ በፍጥነት ለማስተካከል እርምጃ መውሰዱን ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።

የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ከከተማ አስተዳደሩ እርምጃ ጎን ለጎን ጨዋታው ለተመልካች ክፍት እንዲሆን ባደረገው ከፍተኛ ጥረት እንዲሁም የካፍ ሴኪዩሪቲ ኦፊሰር በአካል ተገኝተው ከገመገሙ በኋላ በላኩት ሪፖርት መሰረት ካፍ 10 ሺህ ተመልካች በስታዲየም ተገኝቶ እንዲከታተል ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል።

የሁለቱ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ ነገ ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም