ቀጥታ፡

በእርግዝና ወቅትና ከወሊድ በኋላ በእናቶች ላይ የሚከሰት የጤና እክልን ለመከላከል ትኩረት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2018 (ኢዜአ)፦ በእርግዝና ወቅትና ከወሊድ በኋላ በእናቶች ላይ የሚከሰትን የጤና እክል ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።  

የጤና ሚኒስቴር በእርግዝና ወቅትና ከወሊድ በኋላ ከሚከሰቱ ጤና ችግሮች መካከል አንዱ የሆነው የአዕምሮ ጤና እክል  የሚያጋጥማቸውን እናቶች ጤና መጠበቅ ላይ ትኩረት ያደረገ አውደ ጥናት አካሂዷል።

በቤልጂየም ትሮፒካል ሜዲሲን ኢኒስቲትዩት፣ በአዲስ አበባና ጎንደር ዩኒቨርስቲዎች ትብብር የተዘጋጀው አውደ ጥናትም የአዕምሮ ጤና እክል የሚጋጥማቸውን እናቶች የጤና ደረጃና የመፍትሔ እርምጃዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

በጤና ሚኒስቴር የፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ምርምር መሪ ሥራ አስፈፃሚ ፕሮፌሰር አስቴር ጸጋዬ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ የእናቶችና ህጻነትን ሞት ለመቀነስ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት አምጥተዋል።

እናቶች በእርግዝና ወቅትና ከወሊድ በኋላ የሚያጋጥማቸው የአዕምሮ ጤና እክልም ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በእርግዝና ወቅትና ከወሊድ በኋላ ለሚከሰት የአዕምሮ ጤና እክል ተጋላጭነትን ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ለዚህም የባለድርሻ አካላት፣ ከፍተኛ የትምህርት፣ የጥናትና ምርምር ተቋማት ቅንጅት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና የአዕምሮ ጤና ዴስክ ኃላፊ ዶክተር ሰላማዊት አየለ፤ በእርግዝናና ከወሊድ በኋላ ከቀላል እስከ ከባድ የሚደርስ የአዕምሮ ጤና እክል የሚያጋጥማቸው እናቶችን በተመለከተ በማህበረሰቡ ዘንድ በተሳሳተ ግንዛቤ ችግሩን ተፈጥሯዊ አድርጎ ይወሰዳል።

ይህም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭነታቸውን እንደሚያባብስ አስረድተው፤ ለዚህም በጤና ባለሙያዎች የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በቤልጂየም ትሮፒካል ሜዲሲን ኢኒስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አንተነህ አሰፋ እንደገለጹት፤ የእናቶችን በእርግዝናና ከወሊድ በኋላ የጤና ችግሩን ለመቀነስ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህም በዘርፉ የመጡ ውጤቶችን በማስቀጠል የጥናትና ምርምር እንዲሁም የዲጂታል ቴክኖሎጂ የትብብር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም