ኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓቷን በዓለም አቀፍ አጋርነት ለማዘመን ቁርጠኛ ናት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓቷን በዓለም አቀፍ አጋርነት ለማዘመን ቁርጠኛ ናት
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓቷን ጠንካራ ዓለም አቀፍ አጋርነት በመፍጠር ለማዘመን በቁርጠኝነት ትሰራለች።
በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ በኔዘርላንድስ ሄግ ስትራቴጂካዊ የስራ ጉብኝት እያደረገ ነው።
ልኡኩ ከፍተኛ እውቅና ካላቸው ዓለም አቀፍ የህግ ተቋማት ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን እያካሄደ ይገኛል።
ልዑኩ ከዓለም አቀፉ ቋሚ የግልግል ዳኝነት ፍርድ ቤት (Permanent Court of Arbitration) እና ከሄግ ዓለም አቀፍ የሕግ አካዳሚ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋርም ተወያይቷል።
የውይይቶቹ ዋነኛ ትኩረትም በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ክልል እየተከናወነ ለሚገኘው የፍትህ ዘርፍ ማሻሻያ ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጠናከርና ቴክኒካዊ ድጋፎችን ማግኘት እንደሆነ ተመላክቷል።
ጉብኝቱ ኢትዮጵያን በቀጣናው የግልግል ዳኝነት ማዕከል የማድረግ አካል ሲሆን በአማራ ክልል ዘመናዊ እና ማዕከላዊ የፍትህ ተቋምን የመገንባት እቅድ ተሞክሮ የመውሰድ ውጥንም ያለው ነው።
ከፍተኛ ባለስልጣናቱ በውይይቶቹ ላይ ኢትዮጵያ በጠንካራ ዓለም አቀፍ አጋርነት የሕግ እና ዳኝነት ስርዓቷን ለማዘመን ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
በተጨማሪም ልዑኩ በሄግ የሚገኘውን ታሪካዊ የሰላም ቤተ መንግስት (historic Peace Palace) የጎበኙ ሲሆን ይህም የኢትዮጵያ የፍትህ ዘርፍ የማሻሻያ ጉዞ አስመልክቶ ልምድ የተቀሰመበት እንደሆነም ተመላክቷል።
ጉብኝቱ ኢትዮጵያ ያላትን ዓለም አቀፍ የሕግ ትስስር እና የፍትህ ዘርፍ ሪፎርሙን ወደፊት ለማራመድ የሚያስችል እርምጃ መሆኑ ተገልጿል።
በውይይቶቹም ከአቶ አለምአንተ አግደው በተጨማሪ በቤልጅየም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ፍርቱና ዲባኮ ፣ የኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ማኔጅንግ ዳይሬክተር ኢንጂነር አንዋር ካሳሁን እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሙዎች ተሳትፈዋል።