ባስመዘገብነው የመጀመሪያ ድል ሳንዘናጋ የመልሱን ጨዋታ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንገባለን - አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ - ኢዜአ አማርኛ
ባስመዘገብነው የመጀመሪያ ድል ሳንዘናጋ የመልሱን ጨዋታ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንገባለን - አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ
ድሬዳዋ፤ መጋቢት 21/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ላይ ባገኘው ድል ሳይዘነጋ የመልሱን ጨዋታ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንደሚገባ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ተናገሩ።
አሰልጣኝ ዮሐንስ ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ የሚደረገውን የመልስ ጨዋታ አስመልክቶ ዛሬ በድሬዳዋ ስታዲየም ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
አሰልጣኙ በመግለጫቸው ዋልያዎቹ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታን ለማሸነፍ የሚያስችላቸውን ዝግጅት አድርገዋል ሲሉ ገልጸዋል።
ዋልያዎቹ ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር ሞሮኮ ላይ ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ 3 ለ 0 ማሸነፋቸውን አስታውሰው፤ ይህ ውጤት በምንም መንገድ መዘናጋት ሳይፈጥር ነገ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንገባለን ብለዋል።
የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች በጥሩ የማሸነፍ መንፈስ ታጅበው እንደሚጫወቱ ተናግረዋል።
ተጫዋቾቹ በቂ ልምምድ ማካሄዳቸውንና በስነ-ልቦናም ጭምር ማሸነፍ የሚያስችላቸውን ዝግጅት ማድረጋቸውንም ነው የገለጹት።
በአባቱ ድንገተኛ ህልፈት ምክንያት በመጀመሪያው ጨዋታ ያልነበረው የቡድኑ አምበል ጋቶች ፓኖም ለመልሱ ጨዋታ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በመቀላቀል ልምምድ ማድረጉን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነገ ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር የሚካሄደውን የ36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ካሸነፈ ወደ ምድብ ድልድሉ ይቀላቀላል።
36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምስራቅ አፍሪካ አገራት በሆኑት ኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳ ጣምራ አዘጋጅነት እ.አ.አ ጁን 2027 ይካሄዳል።