የአፋር ክልልን የቱሪስት መዳረሻዎች የበለጠ ለማልማት እና ለማስተዋወቅ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፋር ክልልን የቱሪስት መዳረሻዎች የበለጠ ለማልማት እና ለማስተዋወቅ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ሰመራ፤ መጋቢት 21/2018 (ኢዜአ)፦ የአፋር ክልል የቱሪስት መዳረሻዎችን የበለጠ ለማልማት እና ለማስተዋወቅ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።
የአፋር ክልል ቱሪዝም ቢሮ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማስተዋወቅና በማልማት ረገድ ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።
የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ሁመድ እንደገለጹት የተደረገው ስምምነት ዘርፉን የበለጠ ለማስተዋወቅና ለማልማት ትልቅ እገዛ ያደርጋል።
ስምምነቱ የአፋር ክልልን የቱሪዝም መዳረሻዎች ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችሉ በምርምር ላይ የተመሰረቱ ሥራዎችን ለማከናወንም ያግዛል ብለዋል።
ቢሮው ዘርፉን የበለጠ ለማሳደግ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት የሚያጠናክሩ እንቅስቃሴዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም በዘላቂነት ለማሳደግ የሚያስችል አሰራር ለማዘመን የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መሐመድ ኡስማን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚቆየው ስምምነቱ የአፋርን ክልል ቱሪዝም ለማሳደግ ቁልፍ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው ሁሉን አቀፍ የቱሪዝም ልማት ስትራቴጂ ማዘጋጀት፣ የቱሪስት መስህብ መረጃዎችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዙ ማድረግ እንዲሁም ዘመናዊ የቱሪስት መዳረሻ ካርታ እና የማስተዋወቂያ ሥራዎችን ያከናውናል ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ ስምምነቱ የቱሪዝም ልማትን በምርምር ሥራዎች በመምራት ዓለም አቀፍ ደረጃውን እንዲጠብቁ ለማድረግም እንደሚያግዝ አመልክተዋል።