የቻይና የፋይናንስ ተቋማት ለኢትዮጵያ የልማትና ኢኮኖሚ ማሻሻያ ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋገጡ - ኢዜአ አማርኛ
የቻይና የፋይናንስ ተቋማት ለኢትዮጵያ የልማትና ኢኮኖሚ ማሻሻያ ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋገጡ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2018 (ኢዜአ)፦ የቻይና የፋይናንስ ተቋማት ለኢትዮጵያ የልማትና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ።
በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ልዑክ በቻይና የስራ ጉብኝት እያደረገ ነው።
ልዑኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ያካተተ ነው።
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበውም የተገኙ ሲሆን፤ የልዑኩ ጉብኝት ሁለት አላማዎችን ያነገበ ነው።
ይህም በሂደት ላይ ያለውን የዕዳ ሽግሽግ ድርድር ማጠናቀቅ እና ለቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ግንባታ የሚውል የፋይናንስ ስምምነቶችን ማፋጠን ላይ ትኩረቱን አድርጓል።
ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የቆየ የኢኮኖሚ አጋርነትም ይበልጥ እንደሚያጠናከር ተመላክቷል።
ልዑካን ቡድኑ በቆይታው ከቻይና ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ፣ ከቻይና ኢንዱስትሪና ንግድ ባንክ እና ከቻይና ልማት ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተከታታይ ውይይቶችን አድርጓል።
ውይይቶቹ የዕዳ ሽግሽግ ሂደቱን በማጠናቀቅና ለኢትዮጵያ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንቶች አዲስ የፋይናንስ ምንጭ ለማግኘት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በዕዳ ሽግሽግ ድርድሩ ላይ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን ገልጸው፤ ሂደቱ አሁን ላይ የማጠቃለያ ምዕራፍ ላይ መድረሱን አመልክተዋል።
ይህ ሂደት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቅ ለመንግስት አስፈላጊውን የበጀት ነፃነት በመፍጠር፣ ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችንና ዕድገት ተኮር የልማት ተግባራትን ለማፋጠን እንደሚያስችል ተናግረዋል።
የቻይና የፋይናንስ ተቋማት በበኩላቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ውጤቶች አድንቀዋል።
መንግስት በዕዳ ሽግሽግ ሂደቱ ላይ እያሳየ ያለውን ገንቢ ተሳትፎና የተመዘገበውን ስኬት በማድነቅ፣ ለኢትዮጵያ የልማትና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጥረት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ በድጋሚ አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም ሚኒስትሩ የኢትዮጵያና የቻይናን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ጥንካሬ በማንሳት፣ የፋይናንስ ተቋማቱ ለቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የሚውለውን የፋይናንስ ማዕቀፍ የመገምገምና የማጽደቅ ሂደት እንዲያፋጥኑ ጥሪ አቅርበዋል።
ፕሮጀክቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ፋይዳና አዋጭነት ያለው መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ይህም ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን የአቪዬሽን ማዕከልነት ለማጠናከርና ለረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ሽግግር ቁልፍ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።
ሁለቱ ወገኖች በመሠረተ ልማት ፋይናንስና ኢኮኖሚ አጋርነት ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከርም ተስማምተዋል።
ይህም በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የቆየና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግር የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።