በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ሃይል ወታደራዊ አዛዥ ኮማንዶ ፍቅሩ ሙሉዬ የመንግስትን የሠላም ጥሪ ተቀብሎ ገባ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ሃይል ወታደራዊ አዛዥ ኮማንዶ ፍቅሩ ሙሉዬ የመንግስትን የሠላም ጥሪ ተቀብሎ ገባ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2018 (ኢዜአ) ፦ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰውና ራሱን አፋብን ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ሃይል ወታደራዊ አዛዥ ኮማንዶ ፍቅሩ ሙሉዬ ከመንግስት የተደረገለትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ከነአጃቢዎቹ ላሊበላና አካባቢው ወደ ሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት በሰላም ገብቷል።
አማራን ነፃ እናወጣለን የሚል መነሻ ይዘን ትግል ብንጀምርም አሁን ላይ ሰከን ብለን ሁኔታውን ስንመለከተው አካሄዳችን የአማራን ህዝብ እና ሀገራችንን ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ ሆኖ ስላገኘነው እና መነሻችንን ስተን የትግል ሂደታችን የከፋ ደረጃ ላይ በመድረሱ የሠላም ጥሪ ተቀብለናል ብሏል።
አላማችን በውስጣችን ባሉ አድር ባዮች ፣ በህወሓት እና በውጭ ሀይሎች ተጠልፏል ያለው ኮማንዶ ፍቅሩ እኔ የታሪክ አተላ ተሳታፊ መሆን ስለማልፈልግና የህወሓት ፍላጎት አስፈፃሚ ባለመሆኔ መንግስት ያደረገልኝን የሠላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላማዊ ህይወት ተመልሻለሁ ሲል እውነታውን አስረድቷል።
ችግሮች ቢከሰቱም በሰላማዊ መንገድ ብቻ መፍታት ትክክለኛ አማራጭ መሆን እንዳለበት እምነቱን ገልፆ ባልሰከነ ግንዛቤ ተገፋፍቼ ህዝብን እና ሀገርን መበደሌ ፀፅቶኛል ሲልም ተናግሯል።
ከእንግዲህ ካለፈው ስህተት ተምሬ ሀገሬን እና ህዝቤን ለመካስ ዝግጁ በመሆን ወደ ሰላማዊ ትግሉ ተቀላቅያለሁ ያለው ኮማንዶ ፍቅሩ ሙሉዬ ሁሉም በጫካ የሚገኙ አባላት የመንግስትን የሠላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።
በአማራ ክልል የሚሥተዋለውን ግጭት በማሥቀረት ክልሉን ከጦርነት ቀጣና ወደ ልማታዊ እንቅስቃሴ ማሸጋገር እንደሚገባም አንስቷል።
የሀገራችንን እና የህዝባችንን ሰላም ማረጋገጥ ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን ያሠመረበት ኮማንዶ ፍቅሩ ሙሉዬ ለኢትዮጵያ የእድገት ማነቆ ሆነው የቀጠሉ ጠላቶቻችንን በጋራ ለመመከት ዝግጁ መሆኑን በአሥተያየቱ አሥረድቷል።
ውሳኔው በክልሉ የሚታየውን አለመረጋጋት በውይይትና በድርድር መፍትሄ ለመፈለግ ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይጠበቃል ሲል መረጃውን ያደረሠን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ነው።