ቀጥታ፡

በክልሉ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በጋራ መከላከል ይገባል

 ጅግጅጋ፤ መጋቢት 21/2018 (ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በጋራ መከላከል እንደሚገባ የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ገለጸ።

በሶማሌ ክልል በሴቶችና በህጻናት ላይ የሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን የመከላከል ተግባርን ለማሳካት ያለመ ውይይት ተካሂዷል።

የሶማሌ ክልል ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ሃላፊ ሀሊሞ ሀሰን በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ በሴቶችና በህጻናት ላይ የሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የባለ ድርሻ አካላት ተሳትፎ መጠናከር አለበት።

በክልሉ የሴቶች ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፤ ይሁንና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አሁንም የዘርፉ ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመዋል።

ችግሩን በመፍታት ሁለንተናዊ ተሳትፏቸውን ለማጉላት ከምንግዜውም በላይ ለቅንጅታዊ አሰራር ትኩረት መሰጠቱን  አመልክተዋል።

የሶማሌ ክልል ሸሬአ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ አህመድ ሃዲ ሴቶች  በጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ተጎጂ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ  ችግሩን ለመፍታት በሚደረጉ ጥረቶች የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን አመልክተዋል።

የሶማሌ ክልል ፍትህ ቢሮ  የቅሬታ የምርመራና ክስ ምስረታ የሥራ ሂደት ሃላፊ አቶ አብዲ አደን እንደገለጹት፣ በህገ-መንግስቱ የተደነገገውን የሴቶችና የህጻናት መብት መጠበቅ  አስገዳጅ መሆኑን ገልጸዋል።

በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና ወንጀሎችን ለመከላከል የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ሃዎ ሱሌማን በበኩላቸው በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ያለ እድሜ ጋብቻ   በጤናቸው ላይ  ጉዳት  የሚያደርሱ በመሆናቸው  በጋራ መከላከል ይገባል  ብለዋል።

በመድረኩ ላይ  የሃይማኖት አባቶች፣ የፍትህ አካላትና ሌሎች  የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም