በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተሞች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ማረጋገጥ የሚያስችል የመሰረተ ልማት ግንባታ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተሞች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ማረጋገጥ የሚያስችል የመሰረተ ልማት ግንባታ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2018 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተሞች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ማረጋገጥ የሚያስችል ዘመናዊ የመሰረተ ልማት ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
በከተሞቹ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ የዲስትሪቡሽን መስመር መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት በመከናወን ላይ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ የኃይል ማከፋፈያ ኔትወርክ ጥራትን ለማሻሻል የሚያግዙ ከኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚወጡ መስመሮችን መልሶ መገንባትና ማሻሻል፤ እንዲሁም ከፈቃድ በላይ የሆነ የኃይል ፍጆታን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ 62 የሎድ ብሬክ ስዊቾችን መግጠምን ያካትታል።
የሚገነቡት መስመሮች በኮንክሪት ምሰሶዎች እና በሽፍን ኬብል የሚከናወኑ በመሆናቸው ለአደጋ የማይጋለጡና ለረጅም ዓመታት አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ናቸው ተብሏል።
የአዲስ አበባ ዲስትሪቢውሽን ሪሃቢሊቴሽን 4ኛ ምዕራፍ ፕሮጀክት ሃላፊ ቅድስት ላቀው ለኢዜአ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ በዋናነት የኃይል ኔትወርክ እድሳትን እና የመስመሮችን አስተማማኝነት ማረጋገጥን ዓላማ ያደረገ ነው።
በዚህም 2 ሺህ አዲስ የተለያየ አቅም ያላቸው ትራንስፎርመሮች ተከላና 2 ሺህ ነባር ትራንስፎርመሮች አቅም የማሳደግ ሥራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡
በፊዩዝ የነበረ ትራንስፎርመር ወጪ በዲስትሪቢዩሽን ቦክስ እንደሚሆን ተናግረው ይህም የሚቆራረጡ መስመሮች በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተሞች 673 ኪሎሜትር የሚሆን መስመሮች እንደሚቀየሩ ገልጸው፤ ሽፋን የሌለው የኤሌክትሪክ መስመር ገመዶች እንደሚቀየሩና የኤሌክትሪክ መቆራረጥን እንደሚያስቀር ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ አስተማማኝ የሀይል አቅርቦትን ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።
የቻይና ኢነርጂ ግሩፕ ምክትል ማናጀር ሁ ዊሚንግ ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን የማቆም ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ የማገናኘት እና የሙከራ ስራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በፕሮጀክቱ የሎት አንድ ሳይት መሀንዲስ አረአያ ጌታሁን በምስራቅ ሪጅን ካሉ ሳይቶች ውስጥ ሶስቱ መጠናቀቃቸውን ገልጸው፤ በተያዘለት ጊዜ ማጠናቀቅ የሚያስችል ስራም እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።