ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ወደ ማህበረሰቡ ለማድረስ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ነው

ሮቤ፤ መጋቢት 21/2018(ኢዜአ)፦ መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ወደ ተጠቃሚው ማህበረሰብ እንዲደርሱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገለጸ።  

ዩኒቨርሲቲው ይህንን የገለጸው ''ምርምር ለማህበረሰብ ለውጥና ዘላቂ ልማት'' በሚል መሪ ሀሳብ ዓመታዊ የምርምር ኮንፍረንስ እያካሄደ ባለበት ወቅት ነው።  

በመርሐግብሩ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች፣ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት በዛብህ ወንድሙ እንደገለጹት፤ ተቋሙ ከመማር ማስተማር ተግባር ጎን ለጎን የማህበረሰቡን ችግርና ፍላጎት መሰረት ላደረጉ ጥናትና ምርምሮች ልዩ ትኩረት ሰጥቷል።  

ዩኒቨርሲቲው በዋናነት በግብርና እና ምርታማነት፣ በቱሪዝም ልማት፣ በጤና ጥበቃ እና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።  

ቀደም ሲል በተናጠል ይከናወኑ የነበሩ ጥናቶች አሁን ላይ ተቀናጅተው ጠንካራ ውጤት እንዲያመጡ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።  

በዚህ ዓመታዊ አውደ ጥናት ላይም በተለያዩ ዘርፎች የተጠኑ 42 የምርምር ውጤቶች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጸዋል።  

ጥናቶቹ በወረቀት ላይ ብቻ እንዳይቀሩ ከመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅት መፈጠሩን ምክትል ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል።  

ይህም የጥናትና ምርምር ውጤቶች ወደ ማህበረሰብ ፕሮጀክት ተቀይረው ህዝቡን በቀጥታ ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ያስችላል ብለዋል።  

በትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራ አስፈጻሚ ሰራዊት ሀንድሶ(ዶ/ር) በበኩላቸው በበይነመረብ (ቨርቹዋል) ባስተላለፉት መልዕክት፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን የምርምር ውጤቶች ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ የጀመሩትን ጥረት ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።  

ለዚህም ተመራማሪዎች አቅማቸውን በማጎልበትና ምቹ መደላድሎችን በመጠቀም ውጤታማ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።  

የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎችም እንዲህ ያሉ መድረኮች ተመራማሪዎችና ተጠቃሚ አካላት ተቀራርበው በችግሮች ላይ እንዲመካከሩ በማድረጋቸው፣ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ጉልህ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም