መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወጪን የቀነሰ እና እንግልትን ያስቀረ ዘመናዊ አገልግሎት ነው - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወጪን የቀነሰ እና እንግልትን ያስቀረ ዘመናዊ አገልግሎት ነው
ሐረር፤ መጋቢት 21/2018 (ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወጪን የቀነሰ እና እንግልትን ያስቀረ ዘመናዊ አሰራር መሆኑን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናገሩ።
በሐረር ከተማ እየተሰጠ ያለውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልገሎት በተመለከተ ኢዜአ ተገልጋዮችን፣ ሰራተኞችንና የሚመለከታቸውን የስራ ሃላፊዎች አነጋግሯል።
አገለገሎት ሲጠቀሙ ካገኘናቸው ደንበኞች መካከል ወጣት ግርማ ተክሌ፤ በማዕከሉ በፍጥነትና በጥራት አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ወጪንና እንግልትን ያስቀረ፤ በዘመናዊ አሰራር የታገዘ መሆኑም እንዳስደሰታቸው ጠቅሰው፤ የተለያዩ ጉዳዮችን በአንድ ማዕከል በጥራትና ፍጥነት ማግኘት መቻል አዲስ የስራ ባህል ስለመሆኑም አንስቷል።
ሌሎች ሲገለገሉ ያገኘናቸው አቶ ወንድዬ ዳሳለኝ እና አቶ ሙሉጌታ ታዬ፤ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጡ ዘመናዊ መሆኑን ገልጸዋል።
የተለያዩ ጉዳዮችን አንድ ማዕከል ላይ በጥሩ መስተንግዶ አጠናቅቆ መመለስ መቻል የሚደነቅ አሰራር መሆኑን ጠቅሰው፤ ተገልጋዮቹ ይህንን አሰራር መንግስት ተግባራዊ በማድረጉ አመስግነዋል።
በመሆኑም መሰል የአገልገሎት አሰጣጦች በሁሉም ከተሞች ቢተገበሩ የገንዘብ ወጪን የሚቀንስ፣ እንግልትንና ብልሹ አሰራርን የሚያስቀር ይሆናል ብለዋል።
የሐረር ከተማ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ሃላፊ አክረም መሀመድ፤ በማዕከሉ አሁን ላይ 35 የተለያዩ የአገልግሎቶች እየተሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በርካታ ተገልጋዮች ያለውጣ ውረድ እየተስተናገዱ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በቀጣይም ተቋማትንና የአገልግሎት አይነቶችን ለመጨመር ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
የሐረር ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተመርቆ ለአገልገሎት ክፍት የተደረገው ህዳር 2 ቀን 2018 ዓ.ም እንደነበር ይታወቃል።