ቀጥታ፡

በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

አርባምንጭ፤ መጋቢት 21/2018 (ኢዜአ)፦ በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ቀጥሏል።

በዛሬው ዕለትም ከተለያዩ አካላት በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉም ተመልክቷል።  

ኬር ኢትዮጵያ ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው የተለያዩ አልባሳት፣ የቤት ቁሳቁስና የንጽህና መጠበቂያ ዕቃዎችን ጨምሮ ሌሎች መገልገያ ዕቃዎችን ድጋፍ አድርጓል።

የኬር ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ማሄ ተሜ (ዶ/ር) አደጋው ባስከተለው ሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብት ውድመት ማዘናቸውን ገልጸዋል።

በአደጋው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ወገኖች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ የሚደረገው ድጋፍ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 10 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የባንኩ ሠራተኞች ማህበርና የሶዶ ዲስትሪክት ሠራተኞች የላኩትን 1 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ድጋፍ ለጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አስረክበዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አልሰን አሰፋ በደረሰው አደጋ ማዘናቸውን ገልጸው ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ ተደጋግፈን ልናልፈው ይገባል ብለዋል።

በሌላ በኩል ቪታ ኢትዮጵያ በበኩሉ 400 ሺህ ብር የሚገመት የቤት ቆርቆሮ፣ ምስማርና ሶላር አምፖሎችን እንዲሁም የኢትዮጵያ አማኑኤል ህብረት ቤተክርስቲያንና የልማት ቢሮው በጋራ 150 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ደምስ አድማሱ አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያውያን የተለያየ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸው ለተደረገው ድጋፍም በዞኑ ህዝብ ስም አመስግነዋል።

ለተፈናቃዮች ሰብዐዊ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም