በዞኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ለመስኖ ልማት መስፋፋት አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ለመስኖ ልማት መስፋፋት አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል
ጎንደር መጋቢት 21/2018 (ኢዜአ) :-በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተካሄደው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ስራ የከርሰ ምድር ውሃ አቅርቦትን በማሻሻል ለበጋ መስኖ ልማት መስፋፋት አመቺ ሁኔታ መፍጠሩን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡
በአማራ ክልል የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራው ከ2003 ዓ/ም ጀምሮ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ይገልፃል።
የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃውም የአፈር ክለትን በመቀነስ ውሃማ አካላትና የመስኖ መሰረተ ልማት በደለል እንዳይሞሉ በማድረግ የሰብል፣ የእንስሳትና ፍራፍሬ ምርታማነትን ለማሳደግ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል።
የመምሪያው ሃላፊ አቶ ንጉሴ ማለደ ለኢዜአ እንደገለጹት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት የለም አፈር መከላትን በማስቀረት ለሰብል ምርታማነት ማደግ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
ይህም የከርሰና ገጸ ምድር ውሃ አቅም እንዲጨምር በማድረግ አርሶ አደሩ በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ በመስኖ በማምረት የምግብ ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥ እየረዳው መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ ከአምስት ሄክታር በታች የነበረውን ዓመታዊ የመስኖ ልማት ስራ አሁን ላይ ወደ 40 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ እንዲለማ የሚያስችል ውጤት ማስገኘቱን አስረድተዋል፡፡
በዞኑ ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ተጠብቀው እየለሙ የሚገኙ ተፋሰሶች ቁጥር 955 መድረሱን ጠቁመው ይህም የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሩ እንዲሳካ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ብለዋል።
አሁን ላይ በንብ ማነብ፣ በእንስሳት ማድለብና በወተት ላሞች እርባታ ለተሰማሩ 1 ሺህ 350 ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዘንድሮ በጋም በድግግሞሽ ከ11 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ባካሄዱት የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ 57 ሺህ 370 ሄክታር የተራቆተ መሬት ላይ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ማከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ሰጠኝ አለነ እንደገለጹት በበጋው የምናከናውነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ስራ በመስኖ፣ በእንስሳትና በሰብል ልማት ምርታማነታቸው እንዲያድግ አስችሏል።
በበጋ መስኖ በመታገዝ በአንድ ሄክታር መሬታቸው ላይ ቲማቲም፣ ሽንኩርትና ጥቅል ጎመን አምርተው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስቻላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የጭልጋ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር እሱባለው መሳፍንት በበኩላቸው በለሙ ተፋሰሶች ላይ በ15 ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች ታግዘው ማር አምርተው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ የህልውናችን መሰረት መሆኑን በመገንዘባችን በልማት ቡድኖች ተደራጅተን በየዓመቱ በግልና በወል መሬቶች ላይ የእርከንና ክትር ስራዎችን እያከናወንን እንገኛለን ብለዋል፡፡