ባለፉት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ መጠነ-ሰፊ ስኬቶች የኢትዮጵያ መጪው ጊዜ ብሩህ ለመሆኑ አመላካቾች ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ መጠነ-ሰፊ ስኬቶች የኢትዮጵያ መጪው ጊዜ ብሩህ ለመሆኑ አመላካቾች ናቸው
አዲስ አበባ፤መጋቢት 21/2018 (ኢዜአ)፦ባለፉት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ መጠነ-ሰፊ ስኬቶች የኢትዮጵያ መጪው ጊዜ ብሩህ ለመሆኑ አመላካቾች ናቸው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የኢኮኖሚ ብልፅግና ክላስተር ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።
በብልፅግና ፓርቲ የኢኮኖሚ ብልፅግና ክላስተር የሴቶችና ወጣቶች የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው።
የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የኢኮኖሚ ብልፅግና ክላስተር ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የመድረኩ ዋነኛ ዓላማ አባላት ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉና የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማስቻል ነው።
ምርጫው ነፃ፣ተዓማኒ፣ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሴቶችና የወጣቶች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ይህም ቅቡልነት ያለው መንግሥት ለመገንባት ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሴቶችንና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አመርቂ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።
ለአብነትም ሴቶች በፓርቲው ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ፣ ወደ አመራርነት እንዲመጡ እና በከተማም ሆነ በገጠር የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በሌላ መልኩ የወጣቶች የፖለቲካና የአመራርነት ድርሻ እንዲያድግ ከመደረጉም በላይ፣በስራ ዕድል ፈጠራ እና በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄና በሌሎችም ዘርፎች ያላቸው ተሳትፎ እንዲጎለብት ተደርጓል ብለዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት አምስት ዓመታት ለህዝቡ የገባውን ቃል ሙሉ በሙሉ ማሳካቱ ለቀጣዩ ምርጫ ትልቅ ስንቅ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በሌሎችም ዘርፎች የተገኙ ውጤቶች መጪው ጊዜ ብሩህ ለመሆኑ አመላካቾች ናቸው ብለዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የክላስተሩ የፖለቲካ ዘርፍ ሰብሳቢ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፤ፓርቲው መሰረታዊ የዜጎችን ጥያቄ ከመመለስ አኳያ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።
የዴሞክራሲ ጥያቄን ለመመለስ የሚያስችሉ ተቋማት መገንባታቸውንና እውነተኛ የዲሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ባለፉት ዓመታት ሀገራዊ አንድነትን ከፍ የሚያደርጉ ስራዎች ተሰርተዋል፤ይህም የዳር ተመልካችነት ቀርቶ ሁሉም ዜጋ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እኩል ተሳታፊ እንዲሆን አስችሏል ብለዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሁሉም እኩል ሜዳ የሚረጋገጥበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ምርጫው ቅቡልነት ያለው የሀገረ መንግስት ግንባታን እውን ለማድረግ እንደሚረዳ አስገንዝበዋል።
ሂደቱንም ሆነ የግቡ ስኬታማነት ለማረጋገጥ በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚና በፖለቲካው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶች መጪው ጊዜ ለብልፅግና ብሩህ እንዲሆን የሚያደርጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።