የተሰማራንበት የፍራፍሬና አትክልት ልማት ተጠቃሚ አድርጎናል-አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የተሰማራንበት የፍራፍሬና አትክልት ልማት ተጠቃሚ አድርጎናል-አርሶ አደሮች
ሀላባ ቁሊቶ፤መጋቢት 21/2018 (ኢዜአ)፦በፍራፍሬና አትክልት ልማት በመሰማራታቸው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ማደጉን በሀላባ ዞን የዌራ ዲጆ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።
የዌራ ዲጆ ወረዳ ከዚህ ቀደም በጎርፍ አደጋና በመሬት ተዳፋትነት ምክንያት ለልማት አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም፣በአሁኑ ወቅት ግን በተከታታይ የአካባቢ ጥበቃ ስራ በመሰራቱ መሬቱ የተሻለ ምርት እየሰጠ መሆኑም ተገልጿል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የወረዳው አርሶ አደሮች እንደገለፁት፥ ቀደም ሲል አካባቢው ዝናብ በዘነበ ቁጥር ለጎርፍ ተጋላጭ በመሆኑ አርሶ አደሩ እርዳታ ጠባቂ ሆኖ ቆይቷል።
በአካባቢው የጎርፍ መቀልበሻ ግንባታ በመከናወኑ እና በሶላር ሃይል የሚሰራ የከርሰ ምድር ውሃ ጥቅም ላይ እንዲውል በመደረጉ፣ አካባቢው ዛሬ ላይ የሌሎች ተሞክሮ መቅሰሚያ ማዕከል ለመሆን በቅቷል ብለዋል።
በኩታ ገጠም በመደራጀት አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ላይ የሚገኙ አርሶ አደሮች "ቀደም ሲል በሴፍቲኔት እርዳታ እንኖር ነበር፤ አሁን ግን በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ምርታችንን ለገበያ በማቅረብ ህይወታችንን እየለወጥን ነው" ብለዋል።
ሌላው የመንገሳ ኢንተርፕራይዝ አባል ዱባለ ሁሴን፤ አምስት ሆነው በተደራጁ በስድስት ወራት ውስጥ በ4 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ገልጿል።
በአካባቢው በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የተሰማራ የእርሻ ድርጅት ስራ አስኪያጅ አደም ኑርአብደላ፤ በ30 ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ ልማት እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፣ ከዚህ ውስጥ በ4 ሄክታር ላይ አቮካዶና ሙዝ በማልማት ውጤት ማግኘት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ልማቱ ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረበ ይገኛል።
የሀላባ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ሀጂ ኑሪዬ እንደገለጹት፥ ወረዳውን ከእርዳታ ጠባቂነት ለማውጣት ሰፊ ስራ ተሰርቷል።
"በ13 ቀበሌዎች ይከሰት የነበረውን ጎርፍ ለመከላከል ከ6 ኪሎ ሜትር በላይ የጎርፍ መቀልበሻ ተገንብቷል ብለዋል።
በተጨማሪም ከ86 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የከርሰ ምድር ውሃን በሶላር ሃይል ለመስኖ እንዲውል ተደርጓል" ነው ያሉት።
ይህም አርሶ አደሩ ከችግር ወጥቶ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልክተዋል።