ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በ11ኛው የአፍሪካ፣ካርቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ንቁ ተሳትፎ አድርጋለች-አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን

አዲስ አበባ፤መጋቢት 21/2018 (ኢዜአ)፦ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በተሳተፉበት 11ኛው የአፍሪካ፣ካርቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ንቁ ተሳትፎ ማድረጓን በቤንሉክስ አገራት እና በአውሮፓ ህብረት ተቋማት የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ገለጹ።

11ኛው የአፍሪካ፣ካርቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ "የተለወጠ እና የታደሰ የአፍሪካ፣ ካርቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት- ተግዳሮት ለበዛባት ዓለም" በሚል መሪ ሀሳብ መጋቢት 19 እና 20 / 2018 ዓ.ም በኢኳቶሪያል ጊኒ ማላቦ ከተማ ተካሂዷል።

በጉባኤው ተገኝተው ንግግር ያደርጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ድርጅቱ ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ውስጥ የአባል ሀገራቱን ጥቅም የሚያስከብር ጠንካራ ድርጅት ሆኖ መቀጠል እንዳለበትም በአፅንኦት ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በንግግራቸው ለድርጅቱ ጥንካሬ ይበጃሉ ያሏቸውን ሀሳቦችም አካፍለዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት በቤንሉክስ ሀገራት እና በአውሮፓ ህብረት ተቋማት የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በመድረኩ የድርጅቱን አስፊላጊነት እና ተፅእኖ ፈጣሪነት የሚያሳድጉ ገንቢ ሀሳቦችን ማካፈላቸውን ተናግረዋል።

እንደ አምባሳደር እሸቴ ገለጸ፥ ኢትዮጵያ የባለ ብዙ ወገን ግንኙነትን የመደገፍ የቆየ እሴትና መርህ ያለት ሀገር ናት።

በዚህም የአፍሪካ፣ካርቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅትን ከመሰረቱ ጥቂት ሀገራት አንዷ መሆኗን ጠቁመው፤ ድርጅቱ እንዲጠናከርም የገንዘብ መዋጮዋን በአግባቡ ከመክፈል ጀምሮ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ማንኛውም ሀገር ብቻውን ሊሰራ የሚችለው ነገር የለም ያሉት አምባሳደር እሸቴ፤ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ያላት ተሳትፎ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር በእጅጉ እንደሚያግዛትም ተናግረዋል፡፡

እነዚህን እድሎች በአግባቡ ለመጠቀም ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት ወጣቶቻቸውን በብዙ መልኩ ማዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።

የአፍሪካ፣ካርቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት እ.አ.አ በ1975 በጆርጅታውን - ጉውያና የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 79 አባል ሀገራት አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም