የሀገረ መንግሥት ግንባታው ምሰሶ የሆኑትን ተቋማት የመገንባትና የማደራጀት ሥራ በልዩ ቁርጠኝነት ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
የሀገረ መንግሥት ግንባታው ምሰሶ የሆኑትን ተቋማት የመገንባትና የማደራጀት ሥራ በልዩ ቁርጠኝነት ተከናውኗል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2018 (ኢዜአ)፦የሀገረ መንግሥት ግንባታው ምሰሶ የሆኑትን ተቋማት የመገንባትና የማደራጀት ሥራ በልዩ ቁርጠኝነት ተከናውኗል ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የኢፌድሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አካታች ፖለቲካዊ ለውጦች ለጽኑ ሀገራዊ መሠረት በሚል መግለጫ አውጥቷል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሙሉ ጽሁፍ እንደሚከተለው ቀርቧል፦
አካታች ፖለቲካዊ ለውጦች ለጽኑ ሀገራዊ መሠረት
የኢፌድሪ መንግሥት ባለፉት የለውጥ ዓመታት አገራችንን ከነበረችበት ስር የሰደደ ፖለቲካዊ ቀውስ አውጥቶ ወደ ተሟላ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር የነደፋቸውን ስልታዊ ግቦች በላቀ ጽናትና ስኬት ወደ ተግባር ቀይሯል።
የዚህ ታሪካዊ ሽግግር ዋነኛ ስኬት ለዘመናት ኢትዮጵያን ሲንድ የነበረውን "የመሐል እና የዳር" አግላይ ፖለቲካዊ ትርክት በመስበር እያንዳንዱ ዜጋና እያንዳንዱ አካባቢ የሥልጣንና የሀብት ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት መገንባቱ ነው።
ይህ ለውጥ ኢትዮጵያ የጥቂቶች ሳይሆን የሁላችንም የጋራ ቤት መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ መሠረታዊ ድል ነው።
ለዘላቂ ሰላምና ለአገራዊ ህልውና መረጋገጥ በትውልዶች መካከል ድልድይ የሚሆን የወል ትርክት ግንባታ ላይ የተመዘገቡት ድሎች የለውጡ መንግሥት ታላቅ ፖለቲካዊ ስኬቶች ሲሆኑ ሃገራችንን ለዘመናት በቅራኔ ውስጥ ዘፍቀው የቆዩ አግላይ ትርክቶች እንዲከስሙ በማድረግ፣ በምትካቸው የሁላችንንም ታሪክና አሻራ የሚዘክሩ የጋራ ትርክቶች በተግባር እንዲጎለብቱ ተደርጓል።
በዚህም የታሪክና የማንነት መገለጫ የሆኑት የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብና በገበታ ለሸገር፣ ለሀገር እና ለትውልድ መርሐ-ግብር የተገነቡ ግዙፍ የቱሪዝም መዳረሻዎች የጋራ አገራዊ ኩራታችንን ከፍ አድርገውታል።
ብዝኃነትን በውበትነት በመቀበል በብሔራዊ ምክክር መድረክ የቀጠለው ትናንትን የማከም ጉዞም ትናንት በጥርጣሬና በክፍፍል ይናጥ የነበረውን አገራዊ ትርክት ቀስበቀስ በተግባር ወደ ተረጋገጠ 'ወንድማማችነትና የጋራ ብልጽግና' እየመራው ይገኛል።
የሀገረ መንግሥት ግንባታው ምሰሶ የሆኑትን ተቋማት የመገንባትና የማደራጀት ሥራ በልዩ ቁርጠኝነት ተከናውኗል።በተለይም የፀጥታ፣ የፍትሕና የዴሞክራሲ ተቋማት ለሕዝብና ለሕግ ብቻ ተገዥ እንዲሆኑ የተደረገው ሪፎርም ስር-ነቀል ለውጥ አምጥቷል።
በዚህም መሠረት እንደ ምርጫ ቦርድና ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያሉ የዴሞክራሲ ተቋማት በገለልተኛ አመራር እንዲዋቀሩ መደረጉ፣ የመከላከያና የደኅንነት ተቋማት ከአገራዊ ተልእኮ ውጭ ከማንኛውም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዲጸዱ መደረጋቸውና የፍትሕ ሥርዓቱ በነጻነት እንዲሠራ የተዘረጋው አሠራር የተቋማዊ ሪፎርማችን ሕያው ማሳያዎች ናቸው።
ይህ ስር-ነቀል የፖለቲካ ለውጥ በውስጥ መረጋጋትና በአገራዊ መግባባት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ኢትዮጵያ የነበሩባትን የህልውና ሥጋቶች በጽናት እንድትወጣ አስችሏታል።
ሉዓላዊነታችንን በፖለቲካዊ ብስለትና በአመራር ጥንካሬ የማስከበር አቅማችን መጎልበቱ፣ የመንግሥትን የፖሊሲ ማስፈጸም ብቃት ከማሳየቱም በላይ አገሪቱን ወደ ተሻለ የእድገት ምዕራፍ አሸጋግሯታል።
እነዚህ የፖለቲካ ድሎች በውስጥ የታየው አንጻራዊ የሰላም መስፈን፣ የፖለቲካ ምሕዳሩ መስፋትና የተቋማት መጠናከር ቀጥተኛ ውጤቶች በመሆናቸው አገራችን ለምታደርገው የብልጽግና ጉዞ መሰረት እየጣሉ ይገኛል።
በአጠቃላይ እነዚህ የፖለቲካ ትልሞችና የተጨበጡ ፍሬዎች ኢትዮጵያን ወደ አዲስና የተሻለ የዴሞክራሲ ልምምድ አሸጋግረዋታል።
የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፎ ማደግ፣ የመንግሥት ተቀባይነት በሕዝብ ዘንድ ጎልቶ መታየትና የሪፎርም ሥራዎች ስኬታማነት ለብልጽግና ጉዟችን አስተማማኝ ዋስትናዎች እየሆኑ መጥተዋል።
መንግሥት ይህንኑ የዴሞክራሲና የብልጽግና ጎዳና አጠናክሮ በመቀጠል፣ ለትውልድ የምትመች፣ የበለጸገችና ሉዓላዊነቷ የተከበረች ኢትዮጵያን የመገንባት ታሪካዊ ኃላፊነቱን በላቀ ቁርጠኝነት መወጣቱን ይቀጥላል።
መጋቢት 21/2018 ዓ.ም የኢፌድሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት