ዋልያዎቹ ከሞሮኮ መልስ የመጀመሪያ ልምምዳቸውን አድርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
ዋልያዎቹ ከሞሮኮ መልስ የመጀመሪያ ልምምዳቸውን አድርገዋል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር ለሚያደርገው የመልስ ጨዋታ የመጀመሪያ ልምምዱን ማምሻውን በድሬዳዋ ስታዲየም ሰርቷል።
በአባቱ ድንገተኛ ህልፈተ ሕይወት ምክንያት በመጀመሪያው ጨዋታ ያልነበረው የብሔራዊ ቡድኑ አምበል ጋቶቾ ፓኖም ስብስቡን ተቀላቅሎ ልምምድ አድርጓል።
የዋልያዎቹ ተጋጣሚ የሆኑት ሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ዛሬ ከቀትር በኋላ ድሬዳዋ መግባታቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ ማክሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በድሬዳዋ ስታዲየም ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ ከትናንት በስቲያ ሞሮኮ ላይ በተካሄደው የመጀመሪያ ጨዋታ 3 ለ 0 አሸንፋለች።
በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው ብሔራዊ ቡድን በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ ወደ ምድብ ድልድል መግባቱን ያረጋግጣል።
36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እ.አ.አ በ2027 በታንዛንያ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ ጣምራ አዘጋጅነት ይካሄዳል።