ቀጥታ፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሱልጣን አሊሚራህ ሐንፍሬ ቤተ-መንግሥት እና መስጅድን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2018 (ኢዜአ)፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአፋር ክልል አይሳይታ ከተማ የሚገኘውን የሱልጣን አሊሚራህ ሐንፍሬ ቤተ-መንግሥት እና መስጅድን ጎበኙ፡፡

በአፋር ክልል በአይሳይታ ከተማ የሚገኙት የሱልጣን አሊሚራህ ሐንፍሬ ቤተ-መንግሥት እና መስጅድ እርስ በእርስ የተሳሰረ ጥንታዊና ታሪካዊ ፋይዳ ያላቸው ቅርሶች ናቸው።


 

በተለምዶ "ቀይ ፎቅ" ተብሎ የሚጠራው ቤተ-መንግሥቱ ሱልጣል አሊሚራህ ሐንፍሬ ወደ ሥልጣን በመጡ በአምስት ዓመታቸው በ1940 ዓ.ም የተመሠረተ ነው።

ቤተ መንግሥቱ ለረጅም ጊዜ በእድሜ ብዛት ፈራርሶ የቆዬ ሲሆን፥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ በተገኘ ገቢ ታድሶ አሁን ላይ የሱልጣኑ መቀመጫና ሙዚየም ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

በመስጅዱና በቤተ-መንግሥቱ ዙሪያ ያለው አካባቢ ለበርካታ ዓመታት የሱልጣንነት ሹመት የሚከናወንበት ታሪካዊ ስፍራ ነው።

የሱልጣን አሊሚራህ መስጅድም መሠረቱ በሱልጣን አሊሚራህ ሐንፍሬ የተጣለ ቢሆንም ግንባታው ሳይጠናቀቅ ቆይቷል።

ከሠላሳ ዓመታት በኋላ ግንባታው ተጠናቆ በቅርቡ ተመርቋል።


 

መስጅዱ በኢትዮጵያ ደረጃ በስፋቱ ቀዳሚ እንደሆነ የሚነገርለትና የአካባቢውን የቱሪዝም መዳረሻነት በማሳደግ ረገድ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ታሪካዊ ቅርስ ነው።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም