የሥርዓተ-ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ የብዝኃ ሕይወት ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
የሥርዓተ-ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ የብዝኃ ሕይወት ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ያስችላል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2018 (ኢዜአ)፡- የሥርዓተ-ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ የብዝኃ ሕይወት ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ገንቢ ሚና እንዳለው የዘርፉ ምሁራን ገለጹ፡፡
በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ ሕጎችና ደረጃዎች ዴስክ ኃላፊ ወንደሰን ታደሰ፤ ኢትዮጵያ የውኃ፣ የደን፣ የዓየር ንብረት አገልግሎት፣ የቁጥጥርና ቱሪዝም ሥርዓተ-ምኅዳር ብትታደልም በሚገባት ልክ አልተጠቀመችም ብለዋል።
የሥርዓተ-ምኅዳር ጉዳዮች በሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ጉዳዮች በከፍተኛ ጫና ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሥርዓተ-ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የሥርዓተ-ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ በአገልግሎቱ አቅራቢዎችና ተጠቃሚዎች መካከል የጋራ መግባባትን በመፍጠር ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ሥርዓትን ማጠናከር እንደሚያስችልም አስረድተዋል።
የፋርም አፍሪካ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሸዊት አማኑኤል በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን የብዝኃ ሕይወት ሃብቶች ለሕብረተሰቡ ይበልጥ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችል ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የባሌ አካባቢ ማኅበረሰብ ተፈጥሮን በመንከባከብ የሥርዓተ-ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ ተጠቃሚ መሆን መጀመሩን ገልጸው፤ ይህ በሁሉም አካባቢዎች መስፋት እንዳለበት አመላክተዋል።
መንግሥት በአረንጓዴ ዐሻራና በአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ማስመዝገቡን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ያላትን የብዝኃ ሕይወት ሀብት ይበልጥ መለየትና ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ሀብትና ሀይድሮሎጂ መምህር ዓለምአየሁ አባተ (ዶ/ር)፤ የሥርዓተ-ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ አዋጅ ማኅበረሰቡ የሠራበትን እንዲያገኝ በማድረግ የተጠናከረ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ማከናወን ያስችላል ብለዋል፡፡
በባሌ ኢኮሎጂ በ20 ወረዳዎች በመሰማራት እየሠሩ መሆኑን የገለጹት የፋርም አፍሪካ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ ፈይሳ አሰፋ፤ በኢትዮጵያ የካርበን ክፍያ መጀመሩ የሕብረተሰቡን የአካባቢ ጥበቃ ተነሳሽነት ያሳድጋል ብለዋል፡፡
የሥርዓተ-ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ አዋጁ ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የብዝኃ ሕይወት ሀብት ጠብቃ እንድትቆይና ማኅበረሰቡ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ ያስችላል ሲሉም አስገንዝበዋል።