በጅማ ዞን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን የማስፋፋት ተግባር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጅማ ዞን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን የማስፋፋት ተግባር እየተከናወነ ነው
ጅማ፤ መጋቢት 20/2018 (ኢዜአ)፡- በሥነ-ምግባርና በአካል የበቁ ወጣቶችን ለማፍራት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን የማስፋፋት ተግባር በትኩረት እያከናወነ መሆኑን የጅማ ዞን አስታውቋል።
32ኛው መላው የጅማ ዞን ስፖርት ሻምፒዮና በጅማ ከተማ መካሄድ የጀመረ ሲሆን፤ ሻምፒዮናው በእግር ኳስ፣ በማርሻል አርት እና በሌሎች 13 የስፖርት ዓይነቶች ለ15 ቀናት መካሄዱን ይቀጥላል።
የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ ዩሱፍ ሻሮ በዚሁ ወቅት፤ ዞኑ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን በመገንባትና ውድድሮችን በማዘጋጀት በሀገርና በክልል ደረጃ ተወዳዳሪ ብሎም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እየሠራ ነው ብለዋል።
የጅማ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ነጉማ መኮንን እንዳሉት፤ በስፖርት ሻምፒዮናው ከሁሉም የዞንና ወረዳዎች የተውጣጡ 1 ሺህ 800 ወጣቶች እየተሳተፉ ነው።
በውድድሩ ዞኑን ወክለው በክልል ደረጃ የሚሰለፉ ስፖርተኞች እንደሚመረጡም ጠቁመዋል።
ስፖርታዊ ሁነቶችን የምናካሂደው ሰላማችንን አስጠብቀን ስንቀጥል በመሆኑ፤ ለሰላም እና ለሀገር አንድነት ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ይገባል ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል የሥራና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ባይሳ ኩማ ናቸው።