ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ዜጎችን የቤት ባለቤት ለማድረግና የከተማ ፕላንን ለማስጠበቅ ያግዛል የተባለ ደንብ መተግበር ጀመረ   

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ዜጎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ፣ የከተማ ፕላንን ለማስጠበቅና ከተሜነትን ለማረጋገጥ ያግዛል የተባለ ደንብ መተግበር መጀመሩ ተገለጸ።   

በክልሉ ካቢኔ ሕገ-ወጥ የከተማ ቤትን ሕጋዊ ለማድረግ የጸደቀውን ደንብ መነሻ በማድረግ የክልሉ መሬት ቢሮ እና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማብራሪያ ሰጥተዋል።   
 
የክልሉ መሬት ቢሮ ኃላፊ መሰረት አሰፋ በዚሁ ወቅት፤ እንደ ክልል መሬትን በዘመናዊ መንገድ ለማስተዳደር የመሬት አጠቃቀም ፕላን መተግበሩን እና የካዳስተር ሥርዓትን ወደ ትግበራ እየገባ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ሥርዓትን በሚፈለገው መልኩ መተግበር እንዳይቻል የከተሞች ሕገ-ወጥ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንቅፋት መፍጠሩን አንስተዋል።

ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በተለይም ችግሩ ስር የሰደደባቸውን ከተሞች በጥናት በመለየት ሕገ-ወጥ መኖሪያ ቤትን ሕጋዊ ለማድረግ የሚያስችል ደንብ በክልሉ ካቢኔ መጽደቁን አስረድተዋል።   
 
ደንቡ በክልሉ ከተሞች ዜጎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ፣ የከተማ ፕላንን ለማስጠበቅና ከተሜነትን ለማረጋገጥ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።   
 
በሌላ በኩል ሸገር፣ አዳማ እና ቢሾፍቱ ከተሞች ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ሥርዓትን ቀድመው መተግበር በመቻላቸው ደንቡ በእነዚህ ከተሞች ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን አረጋግጠዋል።   
 
ከተሞቹ ዘመናዊ የመሬት አያያዝ የካዳስተር ሥርዓትን እያጠናቀቁ በመሆኑ የመሬት አገልግሎት አሰጣጥን በዲጂታል መንገድ እያከናወኑ ስለመሆኑ ገልጸዋል።   
 
ይህም ከተሞቹ ፈጣን ዕድገት ላይ እንዲገኙ ከማስቻል ባለፈ የገቢ አሰባሰብ ዐቅማቸውን በማሳደግ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እንዲፋጠን ማገዙን ነው ያስረዱት።


 

የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ኃላፊ ጉዮ ዋሪዮ በበኩላቸው፤ ደንቡ ከ2005 እስከ መጋቢት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ያለውን ጊዜ የሚያካልል መሆኑን አስገንዝበዋል።

ከዚህም ባለፈ የከተማ ፕላን በምንም መልኩ የማይጣስ፤ ቆይታውም ከሁለት ዓመት ያልበለጠ ሲሆን ደንቡ ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ባሰፈነ መልኩ የተዘጋጀ መሆኑንም አስረድተዋል።   

በዚህ ደንብ ለመጠቀም የሚያመለክት ማንኛውም ሰው በአንድ ከተማ ውስጥ ከአንድ ሕገ-ወጥ ግንባታ ያልበለጠ ያለው ሰው ብቻ እንዲሆን የሚያስገድድ መሆኑንም አመልክተዋል።   
 
ሌላው የከተማውን ዝቅተኛ መመዘኛ መስፈርት ከግምት ባስገባ መልኩ ለመኖሪያ ቤት የሚሰጥ ቦታ ስፋት ብቻ እንዲጠቀም የሚደረግ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም