ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማትን የሚያበረታታ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረጓ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ አድርጓታል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማትን የሚያበረታታ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረጓ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ አድርጓታል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የአረንጓዴና የታዳሽ ኃይል ልማትን የሚያበረታታ የተሟላ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረጓ በቀጣናው ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንዳደረጋት ተገለጸ።
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም የፖሊሲ ጥናት ማዕከል ኃላፊና በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አማካሪ አሊ ዛፋር፤ የሀገሪቱ የኃይል አቅርቦት ምንጭ የሆነው ታዳሽ ኃይል መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ከውኃ ሀብት የሚመነጨው ኃይል የኢንዱስትሪ ልማትን በማሳለጥ ሀገራዊ የልማት ግቦችን በማሳካት ኢትዮጵያን ከቀጣናው ሀገራት ጋር በኃይል ያስተሳስራል ሲሉም ለኢዜአ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባደረገችው ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ሪፎርም በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም የዋጋ ግሽበት መቀነሱንና የውጭ ምንዛሬ ክምችት መሻሻሉን አንስተዋል።
በቀጣናው ዝቅተኛ የኃይል አቅርቦት ዋጋ ያላት፣ ለኢንቨስትመንት ምቹ እና መንግሥት ለዘርፉ ከፍተኛ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳራሻ እንዳደረጋትም አመላክተዋል።
ሀገሪቱ ያላትን የኢንቨስትመንት ዕድሎች ለማስተዋወቅ የምታደርገውን ጥረት በመጥቀስ፤ መንግሥት በታዳሽ ኃይል የሚመራ አረንጓዴ ልማትን ለማረጋገጥ ያለውን ጽኑ አቋም አድንቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት ትልቅ ትኩረት በመስጠት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንዲበረታቱ እያደረገች መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በአካባቢ ጥበቃና በታዳሽ ኃይል ልማት ግንባር ቀደም መሆኗን ጠቅሰው፤ ሌሎች ሀገራት ሊማሩበት የሚገባ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡