ቀጥታ፡

የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረት ውጤቶች ተመዝግበዋል

አዳማ፤ መጋቢት 20/2018(ኢዜአ)፡- የሴቶችን ተሳትፎና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባዔ ሰዓዳ አብዱራህማን ገለጹ።
 
የኦሮሚያ ሴት አመራር አባላት ፎረም በአዳማ ተካሂዷል። 
 
የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባዔና የፎረሙ ሰብሳቢ ሰዓዳ አብዱራህማን በዚሁ ወቅት፤ ሴቶች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ከማረጋገጥ በተጓዳኝ የፖለቲካ ተሳትፏቸው እንዲጠናከር በተደረገው ጥረት ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል። 



 
በሥራ ላይ ባለው የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛው የሥራ ዘመን 46 በመቶ ያህሉ ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በክልሉ በሕግ ተርጓሚና ሥራ አስፈፃሚ ዕርከኖች የሴቶች ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱንም አመላክተዋል።

ፎረሙ የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። 
 
ፎረሙ ሴቶች በሀገር ግንባታ ረገድ እየተወጡ ያሉትን ሚና ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ በማስቻል ረገድ የድርሻውን እየተወጣ ነው ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ መብራት ባጫ ናቸው።


 

የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነት ዐቅም በማጎልበት ረገድ ፎረሙ የሴቶች የማስፈፀም ዐቅም እንዲዳብር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በዚህም ሴቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 43 በመቶ ለፓርላማ እንዲሁም 42 በመቶ ለጨፌ ኦሮሚያ በዕጩነት መቅረባቸውን ጠቁመዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የዜግነት አገልግሎት እስካሁን 156 ሺህ የመኖሪያ ቤቶችን በመገንባትና በመጠገን ዐቅም የሌላቸው እናቶችንና አጋረጋውያንን ተጠቃሚ ማድረግ ችለናል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም