ፌስቲቫሉ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት የሚጠናከርበትና አብሮነት የሚደምቅበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ፌስቲቫሉ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት የሚጠናከርበትና አብሮነት የሚደምቅበት ነው
ሐረር፤ መጋቢት 20/2018 (ኢዜአ)፡- የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት የሚጠናከርበት፣ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዕሴትና አብሮነት የሚደምቅበት ነው ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
23ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድርና 19ኛው የባህል ስፖርት ፌስቲቫል "የባህል ስፖርቶች ልማት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሐሳብ በሐረር ከተማ ተጀምሯል፡፡
ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በወቅቱ እንዳሉት፤ የኅብረ-ብሔራዊ አንድነትና አብሮነት መጠበቅና መረጋገጥ የባህል ስፖርቶችን አጉልቶ ለማሳየት ጠቃሚ ነው።
የበለጠ እንዲጎለብትም መንግሥት ልዩ ትኩረት እንደሰጠው ተናግረዋል፡፡
የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ መክዩ መሀመድ በበኩላቸው፤ መንግሥት የባህል ስፖርትን ቀጣናዊ ትስስርን ለማምጣት፣ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን ለማጠናከር እየሠራበት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የ2026 የአፍሪካ የባህል ስፖርት ፌስቲቫልን የማስተናገድ ዕድል ማግኘቷንም አውስተዋል።
ይህን ዕድል በመጠቀምም የባህል ስፖርቶቻችንን ለአፍሪካ እህት ወንድሞቻችን ለማስተዋወቅ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ ከ293 በላይ የተመዘገቡ ባህላዊ ስፖርቶችና ጨዋታዎች እንዳሉ በጥናት መለየቱን አረጋግጠዋል።
ይሁን እንጅ የጨዋታ ሕግና ሥርዓት ተዘርግቶላቸው ለውድድር የበቁት ከ11 የስፖርት ዓይነቶች እንደማይበልጡ ጠቁመው፤ በቀጣይ ይህን ለማስፋት እንደሚሠራ አመላክተዋል።
የባህል ስፖርት የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በዘላቂነት በማጠናከር ረገድ ትልቁን ሚና እንደሚጫወት የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሕይወት መሀመድ ናቸው፡፡
በሐረር ከተማ የተጀመረው የባህል ስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል ለ8 ቀናት እንደሚቆይና ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ ከ1 ሺህ 500 በላይ ስፖርተኞች ተሳትፎ እንደሚያደርጉበት ተናግረዋል።