ሕዝቡን ያሳተፉ የፀጥታ ማስከበር ሥራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሕዝቡን ያሳተፉ የፀጥታ ማስከበር ሥራ እየተከናወነ ነው
ገንዳውኃ፤ መጋቢት20/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን ሕዝቡን ያሳተፉ የፀጥታ ማስከበር ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸው ተገለጸ።
በዞኑ በወቅታዊ የሰላምና ልማት ተግባራት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በገንዳ ውኃ ከተማ ተካሂዷል።
የአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኃላፊ ተሾመ አግማስ በዚሁ ወቅት፤ በዞኑ አስተማማኝ ሰላምን በማስፈን የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ የልማትና የፀጥታ ሥራዎች አበረታች ናቸው ብለዋል።
ከሰላም ማስፈን ሥራ ጎን ለጎን የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ፈጥኖ ለመጨረስና አዳዲስ የልማት ሥራዎችን ለማስጀመር የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉንም አንስተዋል።
ሕዝቡ የልማት ሥራዎችን ከጸጥታ ማስከበር ተግባር ጋር በማጣመር ለማስኬድ እያደረጋቸው ያሉ ጥረቶች እንዲጠናከሩም ጠቀዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ በበኩላቸው፤ በእያንዳንዱ ተግባር የሕዝቡን ተሳትፎ በማረጋገጥ የሰላሙና የልማቱ ባለቤት ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ይህን ተከትሎም በዞኑ ያለው ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱንና ኅብረተሰቡን በማሳተፍ እየተከናወነ ያለው የሕግ ማስከበር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።