ድርጅቶች ነዳጅን በቁጠባ መጠቀም የሚያስችሉ አማራጮችን እየተገበሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ድርጅቶች ነዳጅን በቁጠባ መጠቀም የሚያስችሉ አማራጮችን እየተገበሩ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2018 (ኢዜአ)፡- መንግሥት ያስቀመጠውን አቅጣጫና መፍትሔ በመከተል ነዳጅን በቁጠባ እየተጠቀሙ መሆናቸውን የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አካሉ አሰፋ እንዳሉት፤ ተቋሙ ስምሪቱን በአግባቡ ለማካሄድ ነዳጅን በከፍተኛ ቁጠባ መጠቀም የሚያስችሉ አሠራሮችን እየተገበረ ነው።
በዚህም መሠረት የነዳጅ ብክነትን ለመቀነስ ተሳፋሪዎችን አሳፍረው እስከሚጨርሱ አሽከርካሪዎች ሞተር እንዲያጠፉና የትራፊክ መጨናነቅ የሌለባቸው ክፍት መንገዶችን እንዲጠቀሙ መመሪያ ተሰጥቷል ብለዋል።
የግሪን አዲስ (ቬሎሲቲ) ትራንስፖርት ዋና ሥራ አስኪያጅ ግዛው ዓለሙ በበኩላቸው ተሽከርካሪዎቹ በቀን ለሕዝቡ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጡ ውለው ሌሊት ኃይል እንዲሞላላቸው እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም የአገልግሎት ቀጣይነትን ለማረጋገጥ አስችሏል ብለዋል።
ወቅታዊውን የነዳጅ እጥረት ከግንዛቤ በማስገባትና የሀገርን የነዳጅ ወጪ ለመታደግ ድርጅቱ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመነጋገር የስምሪት ቦታና ሠዓቱን በማራዘም አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ነው ያሉት።
ይህ አሠራር በነዳጅ እጥረት ምክንያት የሚፈጠረውን የትራንስፖርት ችግር ለመቀነስ ትልቅ መፍትሔ መሆኑን አመልክተው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የከተማ አውቶቡስ አሽከርካሪ ዮሐንስ አያሌው ሕዝብን በአግባቡ ማገልገል እንደሚገባ ገልጸው፣ የነዳጅ ፍጆታን ለመቀነስ የሚሰጡ መመሪያዎችን መተግበር ከእያንዳንዱ አሽከርካሪ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።
ኅብረተሰቡ ያለውን ነባራዊ የዓለም ሁኔታ በመረዳት በተለይም አውቶቡሶችን የመጠቀም ልምድ ሊያዳብር እንደሚገባ የመከሩት ደግሞ የቬሎሲቲ አውቶቡስ አሽከርካሪ አማኑኤል ቴዎድሮስ ናቸው።
ይህም ጊዜንና ኢኮኖሚን ከመቆጠብ አኳያ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።