ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል የመክፈቻ ስነ ስርዓት በሀረር ከተማ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል የመክፈቻ ስነ ስርዓት በሀረር ከተማ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2018 (ኢዜአ)፦ 23ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና 19ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል የመክፈቻ ስነ ስርዓት በሀረር ከተማ ኢማም አህመድ ስታዲየም እየተካሄደ ይገኛል።
ውድድር እና ፌስቲቫሉ የሚካሄደው "የባህል ስፖርቶች ልማት ለኢትዮጵያ ከፍታ!" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።
ስፖርታዊ ውድድሩ በሀረር ከተማ የተጀመረ ሲሆን በተለያዩ የጎዳና ላይ ትርዒቶችና የማርች ባንድ ሰልፍ ታጅቦ መካሄድ ጀምሯል።
በውድድርና ፌስቲቫሉ መክፈቻ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ፣ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፣ የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ህይወት መሐመድ እና የአፍሪካ ባህል ስፖርቶችና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን አመራሮች፣ የሁሉም ክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች፣ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ከክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች የተወጣጡ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በ11 የስፖርት አይነት በሚካሄደው ውድድርና ፌስቲቫል ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ1500 በላይ ስፖርተኞች እንደሚሳተፉ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ፌስቲቫሉ ህብረተሰቡን በባህል ስፖርት ተሳታፊና ተጠቃሚ ከማድረግም ባሻገር የባህል ስፖርትን ማህበረሰብ አቀፍ የማድረግ አላማ ያለው ነው።
ውድድሩና ፌስቲቫሉ እስከ መጋቢት 27 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።