ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል በሐረር ከተማ ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል በሐረር ከተማ ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2018 (ኢዜአ)፦ 23ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና 19ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ከዛሬ ጀምሮ በሐረር ከተማ ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን እና የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ስፖርታዊ ሁነቱን በጋራ አዘጋጅተዋል።
ውድድሩና ፌስቲቫሉ "የባህል ስፖርቶች ልማት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ የሚደረግ ነው።
በ11 የስፖርት አይነት በሚካሄደው ውድድርና ፌስቲቫል ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ1500 በላይ ስፖርተኞች እንደሚሳተፉ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
በውድድርና ፌስቲቫሉ ላይ ከአፍሪካ ባህል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን የተጋበዙ የክብር እንግዶች ይታደማሉ።
ሁነቱ የኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ብዝሃነት እና አብሮነት የሚተዋወቅበት መሆኑ ተመላክቷል።
ፌስቲቫሉ ህብረተሰቡን በባህል ስፖርት ተሳታፊና ተጠቃሚ ከማድረግም ባሻገር የባህል ስፖርትን ማህበረሰብ አቀፍ የማድረግ አላማ እንዳለው የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል።
መንግስት ለስፖርት ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት በአዲሱ የስፖርት ፖሊሲ አማካኝነት የባህል ስፖርቶችን ለማልማት እየሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል።