ቀጥታ፡

የአፋር ሕዝብ በረሃውን በማለምለምና የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ጥንካሬ በመገንባት አለኝታነቱን ዳግም እያደሰ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2018(ኢዜአ)፦ የአፋር ሕዝብ በረሃውን በማለምለምና የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ጥንካሬ በመገንባት አለኝታነቱን ዳግም እያደሰ ይገኛል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የተንዳሆ መስኖ ልማት የማጠናቀቂያ እና መልሶ ግንባታ ፕሮጀክት ዛሬ መርቀዋል።


 

የአፋር ሕዝብ በረሃውን በማለምለምና የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ጥንካሬ በመገንባት አለኝታነቱን ዳግም እያደሰ ይገኛል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ለእኛ ሉዓላዊነት ማለት ዳር ድንበርን ከመጠበቅ ባሻገር፣ የዜጎችን አንገት የሚያስደፋውን የልመና እጅ ሰብሮ በራስ ምርት መቆም ነው ብለዋል።

የአፋር ሕዝብ ለዘመናት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በንቃትና በጀግንነት ሲጠብቅ የኖረ የቁርጥ ቀን የሀገር ባለውለታ መሆኑንም አውስተዋል።

ለምርቃት የበቃው የተንዳሆ መስኖ ልማት የማጠናቀቂያ እና መልሶ ግንባታ ፕሮጀክት፣ የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ትግላችን የድል ዓርማ ነው ብለዋል።

ለዓመታት ተጓትቶ፣ ተስፋ አስቆርጦና የጎርፍ ሥጋት ሆኖ የቆየውን ግድብ፣ በቆራጥ አመራርና በፈጣን አፈጻጸም ወደ ልማት አውታር መቀየሩን ተናግረዋል።

ይህ ፕሮጀክት ለምድራችን በረከት፣ ለሕዝባችን የብልጽግና ምንጭ እንዲሆን ዳግም ተወልዷል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

እውነተኛ ነጻነትና ምሉዕ ክብር የሚረጋገጠው በራስ ማሳ ላይ በሚለማ ሰብል፣ በራስ ጉልበት በሚገራ ውኃና ከማንም እጅ በማይጠበቅ የዜጎች የዕለት ጉርስ መሆኑንም አመልክተዋል።


 

የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተነሣነውም የዜጋን ክብርና የሀገርን የህልውና መሠረት ለማጽናት ነው የዚህ ዋናዎቹ ዐቅሞቻችን ደግሞ ያልተነካው የበረሃ ለም አፈራችን፣ ውኃችን፣ ትጉህ ሕዝባችንና የመስኖ አውታሮቻችን ናቸው ብለዋል።

ለእኛ መስኖ ማለት የዝናብ ጠባቂነትን ታሪክ መዝጋት ነው፤ መስኖ ተለዋዋጭ የሆነውን የዓለም ጂኦ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውጥረት የምንቋቋምበት ብቸኛውና አስተማማኙ መከታችን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የቆላማ አካባቢዎቻችንን እምቅ ሀብት ማልማትና የዜጎቻችንን ሕይወት በዘመናዊ የኮሪደር ልማት ማሣለጥ የወደፊት ዕጣ ፈንታችንን የመወሰን ጉዳይ እንደሆነም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት።

ቃልን በተግባር፣ ሐሳብን በውጤት እየለወጥን፣ አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩንና ባለ ሀብቱን ያስተሣሠረ የልማት ሠንሰለት በመፍጠር፣ ኢትዮጵያን በምግብ ራሷን የቻለች ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የምትተርፍ የብልጽግና ተምሳሌት እናደርጋታለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም