የተንዳሆ መስኖ መሠረተ ልማት እስከ 60 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም አለው - ኢዜአ አማርኛ
የተንዳሆ መስኖ መሠረተ ልማት እስከ 60 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም አለው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2018(ኢዜአ)፦ የተንዳሆ መስኖ መሠረተ ልማት እስከ 60 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም እንዳለው የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የተንዳሆ መስኖ ልማት ማጠናቀቂያና መልሶ ግንባታ ፕሮጀክትን መርቀዋል።
በዚሁ ወቅት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር)፤ ባለፉት ጥቂት ወራት በጠንካራ የፕሮጀክት አመራር አምስት የመስኖ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ወደ አገልግሎት መግባታቸውን አንስተዋል።
ይህም በፌዴራል መንግሥት ያላሰለሰ ድጋፍና በክልሎች ቁርጠኝነት የተሳካ ነው ብለዋል።
የተንዳሆ ፕሮጀክት ስኬትም የግብርና ምርታማነት የተስፋ ምንጭና የኢኮኖሚ መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በመጠናቀቁ የአካባቢው አርሶና አርብቶ አደሮች ከዝናብ ጥገኝነት ተላቀው በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ በማምረት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለተጀመረው ጥረት ላቅ ያለ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ከ15 ዓመታት በፊት ቢጀመርም የማህበረሰቡ የስጋት ምንጭ ከመሆን ያለፈ ጥቅም ሳይሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል።
የውሃ ፍሰቱን መቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት በአግባቡ ስላልተዘረጋለት ተጨማሪ ችግር እንደነበረበትም ጠቅሰዋል።
አሁን ላይም የፕሮጀክቱን ውስብስብ ችግሮች እንዲቃለሉ በማድረግ ወደ ሥራ መግባቱን አንስተዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የግድቡን ሁኔታ በማጥናት የውሃ ማስተንፈሻ ችግሮች እንዲስተካከሉ መደረጉንና 40 ኪሎ ሜትር የካናል ዕድሳት ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።
ማህበረሰቡንና ካናሎቹን ከጎርፍ ለመከላከልም 27 ኪሎ ሜትር የድጋፍ ግንብ መገንባቱን አስታውቀዋል።
የተንዳሆ የመስኖ መሠረተ ልማት 60 ሺህ ሄክታር የማልማት አቅም እንዳለው ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት 33 ሺህ ሄክታር ለማልማት ዝግጁ ሆኗል ብለዋል።
ከዚህ ውስጥም 23 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ የመስኖ ልማቶች መሸፈኑንም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።