ቀጥታ፡

የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የመደመር መንግሥት አንዱና ዋናው ተልዕኮ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2018(ኢዜአ)፦ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የመደመር መንግሥት አንዱና ዋናው ተልዕኮ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፤ ይህንን ያሉት በአፋር ክልል የሚገኘውን የተንዳሆ መስኖ ልማት የማጠናቀቂያ እና የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክት መርቀው ለአገልግሎት በከፈቱበት ወቅት ነው።


 

የምግብ ሉዓላዊነት ዜጎች በራሳቸው ሀብት፣ ዕውቀትና ጉልበት እንዲሁም እንደ አካባቢው ሥነ-ምኅዳር አመቺነት የተለያዩ ሰብሎችን በማምረት፣ የሥነ-ምግብ ባህላቸው ተጠብቆ እንዲመገቡ ማስቻል መሆኑን አብራርተዋል።

ይህም ኢትዮጵያ በተለይ በስንዴ ልማት ስኬት ማስመዝገቧና ከውጭ የሚገባውን ምርት ማስቆም መቻሉን፣ እንደ ኮቪድ-19 ያሉ ዓለም አቀፍ ቀውሶችን በድል እንድትወጣ ማድረጉንም አንስተዋል።

መንግሥት ግብርናን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ ለመስኖ ልማት ልዩ ትኩረት መስጠቱን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ራሱን ችሎ እንዲቋቋም መደረጉን አስታውሰዋል።

ዘርፉ የበጀትና የፋይናንስ ነጻነት እንዲኖረው በማድረግም፣ መንግሥት በየዓመቱ ለመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ ከ20 ቢሊየን ብር በላይ በጀት እየመደበ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በዚህ ምክንያት ላለፉት 20 ዓመታትና ከዚያ በላይ በፕሮጀክት አፈጻጸም ውስንነት ተጓትተው የቆዩ እንደ መገጭና አርጆ ያሉ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እየተጠናቀቁ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የጎዴ፣ የወልመል፣ የቄጦ፣ የጊዳቦ፣ የታችኛው ርብ እና ከሰም የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው የመንግሥትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።


 

ዛሬ የተመረቀውን የተንዳሆ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ከ15 ዓመታት በፊት ቢገነባም መሠረታዊ የሆኑ የማጠናቀቂያ ሥራዎች ባለመከናወኑ ለጎርፍ ሥጋት ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።

አሁን ላይ በተደረገለት ከፍተኛ ጥገናና የማጠናቀቂያ ሥራ ወደ አገልግሎት መመለሱ ትልቅ ስኬት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል።

መንግሥት መስኖን የኢኮኖሚ ዋነኛ ምሰሶ በማድረጉ የሀገሪቱን የመስኖ ሽፋን ከለውጡ በፊት ከነበረበት 490ሺህ ሄክታር ወደ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊየን ሄክታር ከፍ ማለቱን አንስተዋል።

በመስኖ ሊለማ የሚችል 10 ሚሊየን ሄክታር መሬት መኖሩን ጠቅሰው፤ ከዚህም አብዛኛው የሚገኘው እንደ አፋር ክልል ባሉ ቆላማ አካባቢዎች ነው ብለዋል።


 

የአፋር ክልል ሚሊዮኖችን መመገብ የሚችሉ ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችና ተፋሰሶች ባለቤት መሆኑን ጠቁመው፤ ክልሎች ከተገነቡ የመስኖ መሠረተ ልማቶች ጋር ተናብበው በመሥራት አርሶና አርብቶ አደሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና ባለሀብቶች በስፋት የሚሳተፉበትን ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም